በቦሌ ኤርፖርት እና ሆቴሎች ቋሚ የቱሪስት ታክሲ አገልግሎት ሰጪ ባለንብረቶች እና በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን መካከል የስምሪት አሰራርን መሰረት በማድረግ የተፈጠረው አለመግባባት ወደ ፍርድ ማምራቱ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም መሰረት የቱሪስት ታክሲ ማህበራቱ መጋቢት 25 ቀን 2009 ዓ/ም ተግባራዊ ሊደረግ የነበረውን ስምሪት በመቃወም በ18/07/09 ዓ/ም በቁጥር አ/አ/ት/ባ779/2009 ዓ/ም በተፃፈ ደብዳቤ የወጣው አዲሱ የሜትር ተጋክሲዎች ስምሪት እንዲሰረዝላቸው በማሰብ በስምቱ ላይ በስር ፍርድ ቤት እግድ አውጥተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም በ22/07/09 ዓ/ም በዋለው ችሎት የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከዚህ ፍርድ ቤት ተለዋጭ ትዕዛዛ እስከሚሰጥ ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ባለስልጣን መስሪያ ቤት በ18/07/09 ዓ/ም በተፃፈ ደብዳቤ የሜትር ታክሲዎች የስምሪት ምድብ ድልድልን ተፈፃሚ ሳያደርግ ለጊዜው ታግዷል በማለት ትዕዛዝ ሰቷል፡፡
በዚህም መሰረት ይግባኝ ባይ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን በ04/08/09 ዓ/ም በተፃፈ አቤቶታ እግዱ እንዲነሳ ይግባኝ በማለት ጉዳዩን ወደ ቦሌ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት 2ኛ ፍትሀ ብሔር ችሎት ወስዶታል፡፡
ፍርድ ቤቱ ሁለቱን ወገኖች ሲያከራክር በቦሌ ኤርፖርት ቱሪስት ታክሲዎች በኩል እግዱ ቢነሳ ቀድሞ በቦታው ላይ የምንሰራ ሰዎች ገቢያችንን እናጣለን ማህበራቱና ቤተሰብም ይበተናል በሌላ በኩል ታክሲዎቹን ለማዘመን የባንክ ብድር ለመክፈል ይሳነናል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን በጠበቃው በኩል ባሰማው ክርክር ያቀረቡት ማመልከቻና ይግባኝ ሙሉ በሙሉ ስልጣን አለን ከማለት በስተቀር በስልጣናቸው የተሰጠው እግድ ይነሳልን ከማለት በስተቀር በቂ ምክንያት አላቀረቡም ይላል በቀን 29/09/09 ተፅፎ በቀን 12/10/09 የተነበበው የውሳኔ መዝገብ፡፡
በአጠቃላይ የስር ፍርድ ቤቱ እግዱ እንዲነሳ በይግባኝ ባይ ወይንም በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን ላቀረቡት አቤቶታ እግዱ የተሰጠው በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ነጥብ ለይቶ የቀረበውን ክርክር አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች አናፃር መመርመር ሲገባው ሳይመረምር የደረሰበት ድምዳሜ የሰጠው ትዕዛዝ በአግባቡ ባለመሆኑ በፍትሀ ብሔር ስነ-ስርዓት ህግ ቀጥር 348‹1›መሠረት ተሸሯል ሲል መዝገቡን ዘግቷል፡፡
ዘገባው የነጋሽ በዳዳ ነው

በ3.4 ቢሊዮን ብር ተገንብቶ መስከረም ወር የተመረቀው የኢትዮ ጅቡቲ የምድር ባቡር ከምረቃው በኋላ ባሉት ከ 3 እስከ 6 ወራት ውስጥ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚጀምር መነገሩ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ባቡሩ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ዛሬም ድረስ መደበኛ አገልግሎቱን አልጀመረም፡፡ ለምን ስንል ለኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ተፈራን ባነጋገርንበት ወቅት ባቡሩ የሙከራ ስራውን በወቅቱ ባለመጀመሩ የመደበኛ ስራው መዘግየቱን ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
እስከ አሁን መደበኛ የሚባል ስራውን ያልጀመረው ባቡሩ ስራውን መች ይጀምራል ለሚለው ጥያቄ አቶ ደረጄ ተፈራ በምላሻቸው ጊዜውን በትክክል ማስቀመጥ ያስቸግራል ሲሉ ምላሽ ሰተዋል፡፡
መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የኢትዩ ጅቡቲ የምድር ባቡር አስተዳደር 75 ከመቶ ከኢትዮጵያ ቀሪ 25 ከመቶ የሚሆነውን የንግድ ፈቃድ ከጅቡቲ ማግኘት ችሎአል፡፡
ጅቡቲ ላይ ቆመው የሚገኙት የባቡሩ ዋገኖች አገሪቱን ለኪራይ ኪሳራ እየዳረጉ በሀገር ውስጥ የገቡት ሎኮሞቲቮችም ቢሆኑ ለብልሽት መጋለጣቸው ኪሳራው በማን ይታሰባል ለሚለው ጥያቄ አቶ ደረጄ ተፈራ ጅቡቲን በተመለከተ የጋራ ንብረት ስለሆነ ኪራይ አታስከፍልም በሀገር ውስጥ ያሉትም በዚህ ጊዜ ውስጥ ለብልሽት ስለማይዳረጉ ስጋት የለብንም ሲሉ ምላሽ ሰተዋል፡፡
752 ኪሎ ሜትርን የሚሸፍነው ባቡሩ በሰዓት 120 ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ ቀናትን ይፈጅ የነበረውን ርቀት ወደ 10 ሰዓታት ዝቅ ያደርገዋል የሚል እምነት ተጥሎበታል፡፡
ለሚቀጥሉት 6 ዓመታት ቻይናውያን የሚያስተዳድሩትን ባቡር ለመመረቅ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሀ/ማርያም ደሳለኝ፣የጅቡቲው ፕሬዘዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌህ፣የቶጎ ሪፐብሊክ ፕሬዘዳንት ፋዩሪ ኦሲዙማ እና የቻይና ልዩ ልዑክ ተወካይ ዙሻኦሺ በለቡ ባቡር ጣቢያ መገኘታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ዘገባው የነጋሽ በዳዳ ነው

Friday, 23 June 2017 09:23

ቻይና 100,000 ከረጢት የእርዳታ ምግብ በኬኒያ በድርቅ ለተጎዱ ሰዎች ሰጠች፡፡

በናይሮቢ በተካሄደው እርዳታውን የማስረከብ ስነስርዓት ላይ በአገሪቱ የቻይና አምባሳደር እንዳሉት እርዳታው ቤጂንግ ለአገሪቱ ለመስጠት ካሰበችው 450000 ከረጢት የእርዳታ ሩዝ ውስጥ የመጀመሪያው ዙር ነው፡፡ ቻይና በኬኒያ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የምትሠጠው እርዳታ 517 ሚሊዮን ብር ያወጣል፡፡
እርዳታውን በመረከብ ስነስርዓት ላይ የተገኙት የአገሪቱ State department ተቀዳሚ ፀሐፊ ጆሴፍታ ሙኩቤ እንዳሉት ቻይና ለሕዝባችን ያደረገችው ነገር የሚያስመሰግናት ነው ብለዋል፡፡ አክለውም በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ እና በከፊል በድርቅ በተመቱ የአገሪቱ ክፍሎች አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው 3.5 ሚሊዮን ዜጎች ይገኛሉ፡፡
አገሪቱ የመታው ድርቅ የመኖ እጥረት እንዲከሰትና የወተት ምርቱም እንዲያሽቆሎቁል አግርጎዋል፡፡ በተጨማሪም የመሰረታዊ ምግብ ዋጋ ጨምሯል፡፡ የተከሰተው ድርቅ በውኃ ግኝት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደሩ ምክንያት የሰብል ምርት እንዲያሽቆሎቁል ያደረገ ጭምር ነው፡፡ ከቻይና የተበረከተው እርዳታ ከሞንባሳ ናይሮቢ በተዘረጋው የባቡር መስመር የተጓጓዘ ነው፡፡

Friday, 23 June 2017 09:20

እ.ኤ.አ በ 2050 የአለም ህዝብ ወደ 10 ቢሊዮን እንደሚጠጋ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡

በ 2050 ይኖራል ተብሎ በተገመተው የሕዝብ ቁጥር መሰረት ህንድ ከቻይና እንደምትበልጥና በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛት በቀዳሚነት የተሰለፈችው ናይጄሪያ 2050 ከመግባቱ ጥቂት ግዜ ቀደም ብሎ አሜሪካን በመብለጥ በአለም ሶስተኛ የሕዝብ ብዛት እንደሚኖራት ተገምቷል፡፡
የአፍሪካ 26 አገራት የሕዝብ ቁጥራቸው በእጥፍ እንደሚያድግና በ 2050 የአለም 47 አገሮች ደግሞ 33 በመቶ ወይንም አሁን ካላቸው 1 ቢሊዮን ዜጎች ወደ 1.9 ቢሊዮን እንደሚጨምር የተባበሩት መንግስታት በትላትናው ዕለት ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል፡፡
በዚህ ሪፖርት መሰረት በአለማችን አነስተኛ ወሊድ ያለባቸው አገራት ቻይና፣ አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ራሺያ፣ ጃፓን እና ሌሎችም ሆነውዋል፡፡ 60 እና ከ 60 አመት በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቁጥር አሁን ካለበት 962 ሚሊዮን በእጥፍ በማደግ 2.1 ቢሊዮን እንደሚሆንም ሪፖርቱ አስቀምጧል፡፡
ዘገባው የ News 24 ነው፡፡

Friday, 23 June 2017 09:16

አይ ኤስ (IS) በኢራቅ ሞሱል የሚገኝ ጥንታዊ መስኪድን አወደመ፡፡

የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይደር አላባዲ እራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ የሚጠራው ፅንፈኛ ቡድን በሞሱል ከተማ የሚገኘውን ጥንታዊ መስኪድ ማውደሙ በጦርነቱ ድል እንዳልቀናውና እየተሸነፈ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
አይ ኤስ (IS) የኢራቅ መንግስት ኃይሎች የሚያደርጉትን ግስጋሴ ለማስቆም ውጊያ ባደረገበት ወቅት ነው አል ኑሪ የተሰኘውን ጥንታዊ መስኪድ እንዳወደመውም የተነገረው፡፡ አይ ኤስ (IS) በበኩሉ ጥንታዊ መስኪዱ የወደመው የአሜሪካ አየር ኃይል በሰነዘረው የአየር ጥቃት እንደሆነ ተናግሮዋል፡፡ ከስምንት መቶ አመታት በላይ እንዳስቆጠረ የሚነገርለት ይህ ጥንታዊ መስኪድ ከአየር ላይ በተነሳ ፎቶግራፍ መሰረት በስፋት ወድሞዋል፡፡
በኢራቅ የአሜሪካን ኮማንደር ሜጀር ጀነራል ጆሴፍ ማርቲን እንዳሉት አይ ኤስ (IS) ያወደመው የኢራቅ እና ሞሱል ታላቁን ሐብት ነው፡፡ አክለውም ይህ ድርጊት በኢራቅ እና ሞሱል ህዝብ ላይ የተፈፀመ ወንጀል እንደሆነ ነው ተናግረዋል፡፡
ግንቦት 2 ቀን 2009 ዓ.ም በተጀመረው ዘመቻ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢራቅ ኃይሎች፣ የኩርዲሽ ተዋጊዎች፣ የሱኒ አረቦች እና የሺአ ሚሊሻዎች በአሜሪካ በሚመራው የአየር ላይ ጥቃትና ወታደራዊ ምክር እየታገዙ ቁልፍ ከተማዎችን በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል ውጊያ ላይ ናቸው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አይ ኤስ (IS) ቢያንስ አንድ መቶ ሺህ ሰዎችን በሞሱል በመያዝ እራሱን ለመከላከል እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
ዘገባው የ BBC ነው፡፡

የኢትዮጵያ ምግብ፣ መድኃኒት እና ጤና እንክብካቤ ባለሥልጣን የህክምና አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ከሚመለከት ክፍል የሚመጡ የተለያዩ ጉዳዮችንና መረጃዎችን በማሰባሰብ እና ዶክተሮች ስራቸውን በሚከውኑበት ወቅት ሊያጋጥም የሚችል ስጋትን ከግምት ውስጥ በማስገባት የዶችተሮችና የህክምና ባለሙያዎች ኢንሹራንስ መክፈቱን ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጀነራል ኢንሹራንሽ አስታውቋል፡፡
ከዚህ ቀደም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባስተላለፈው የመጨረሻ ውሳኔ መሰረት በህክምና ወቅት ለተፈፀመ ስዕተት 4 ሚሊዮን ብር በካሳ መልክ ተጠይቆ ከ አንድ ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፈል ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ፍትሃ ብሄር ህግ በህክምና ወቅት ለሚደርስ ስዕተት የህክምና ተቋሙን እና ሠራተኞቹን ተጠያቂ በማድረግ ካሳ እንዲከፈል ያደርጋል፡፡ የተለያዩ አገራትም በህክምና ወቅት ለሚደርስ ስዕተት ካሳ እንዲከፈል እና አስፈላጊ ወጪዎችም እንዲሸፈኑ ያስገድዳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሜዲካል አሶሴሽን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር የኔነህ ጌታቸው እንዳሉት በኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጀነራል ኢንሹራንሽ የተጀመረው የኢንሹራንስ አይነት ለረጅም ግዜ ይጠብቁት የነበረ እና በሙያ ውስጥ ያሉ የህክምና ባለሙያዎችን የሚጠቅም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በእንግሊዝ ሜዲካል ኢንደሚኒቲ ኢንሹራንስ የሌላቸው የህክምና ባለሙያዎች የንግድ ፍቃድ አይሰጣቸውም፡፡