አለም አቀፍ ዜናዎች (169)

Wednesday, 29 October 2014 14:10

የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ሚካኤል ሳታ መሞታቸው ተሰማ፡፡

ጥቅምት 19/2007 ዓ.ም

ዛሬ ማለዳው ላይ ከሀገሪቱ ታማኝ ምንጮች ሰማሁ ብሎ የተናገረው AFP ፕሬዝዳንቱ በእንግሊዝ ለንደን የህክምና ክትትል ያደረጉ በነበረበት ወቅት ነው ህልፈታቸው የተሰማው፡፡

የዛምቢያ ባለስልጣናት ከሉሳካ ምንም ያሉት ነገር የለም የተባለ ሲሆን ዘኢንዲፔንደንት ዛምቢያ  የተባለው የዜና ምንጭ እና የሀገሪቱ የወሬ ምንጮች ትክክለኝነቱን ተናግረዋል፡፡ የሀገሪቱ ፓርላማም መሞታቸውን በይፋ ተናግሯል፡፡

ፕሬዝዳንት ሳታ ከባለፈው ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ስብሰባ በኋላ ከህዝብ አይን እርቀው ነበር የተባለ ሲሆን በሀገሪቱ ማድረግ የሚገባቸውን ህዝባዊ ገለፃም እንዳላደረጉ ተነግሯል፡፡

በፈረንጆቹ መስከረም 19 ቀን ላይ ለሀገሪቱ ፓርላማ አልሞትኩም የሚል መልዕክትም ልከዋል የተባሉት ፕሬዝዳንቱ በለንደን ረዘም ያለን ጊዜ በህክምና ክትትል ሲያሳልፉ እንደነበር የዜና ምንጮች ተናግረዋል ፕሬዝዳንት ሚካኤል ሳታ የ77 ዓመት አዛውንት እንደነበሩም ተነግሯል፡፡ ዘገባው የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ነው፡፡

Tuesday, 28 October 2014 10:53

በላይቤሪያ ይኖሩ የነበሩ ኬንያውያን ከኢቦላ ጋር በተያያዘ ሳይያዙ አይቀሩም በሚል ወደ ሀገራቸው እንዲላኩ ተደረገ፡፡

ጥቅምት 18/2007 ዓ.ም

ካፒታል ኒውስ ዛሬ ባወጣው ዜና እንደተናገረው በላይቤሪያ ይኖሩ የነበሩና በእርዳታ መስጫ ተቋም ውስጥ የተሰማሩ የነበሩት 12 ያህል ኬንያውያን ናቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የተደረገው፡፡

ከ5000 በላይ ምዕራብ አፍሪካውያን በኢቦላ ምክንያት ሞተዋል የሚለው ዘገባው ከእነዚህ መካከል ግማሽ ያህሉ ላይቤሪያውያን እንደሆኑ ተናግሯል፡፡

ኬንያ የአየር በረራን አለማቋረጧን ተከትሎ የህዝቦቿ ስጋት እያየለ እንደመጣ የተነገረ ቢሆንም እስካሁን በተደረገ ምርመራ አንድም ኬንያዊ ላይ ቫይረሱ እንዳልተገኘ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

የሀገሪቱ የጤና ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ እንደተናገሩት ኬንያ በአሁን ወቅት ከኢቦላ ነፃ ከሆኑ ሀገራት ተርታ የምትመደብ ስትሆን ለቱሪስቶችም አስጊ አይደለምች ብለዋል፡፡

አሁን በላይቤሪያ በቫይረሱ ተይዘዋል የተባሉት 12 ኬንያውያን የተለየ ጥበቃ እንደሚደረግላቸውና ከህዝብም እንዳይገናኙ እንደሚደረግ ተያይዞ ተነግሯል፡፡ ዘገባው የካፒታል ኒውስ ነው፡፡

Tuesday, 28 October 2014 10:30

ጋና እና ሱዳን ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከስምምነት ላይ ደረሱ፡፡

ጥቅምት 18/2007 ዓ.ም

በጋና የሱዳን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ባቢኪር ኤልሲደግ ሞሀመድ ኤላሚን የጋና ፖሊስ እና መንግሥት ከሱዳን ፖሊስ እና መንግሥት ጋር በመተባበር ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ያለውን የመከላከልና አዘዋዋሪዎችንም በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በተለይም ከኤርትራ፣ ሱማሊያ እና ኢትዮጵያ የሚገቡ ህገ-ወጥ ስደተኞች ቁጥር ከዕለት ዕለት እየጨመረ ነው ያሉት አምባሳደሩ ወደ ጣልያን እና እስራኤል እንዲሁም ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ለመግባት ሱዳንና ጋናን መሸጋገሪያ ያደርጋሉ፤ ይህ ደግሞ ለሀገራቱ ደህንነት ስጋት ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ጋና ለጎብኚዎች ምቹ እና ሰላማዊ ሀገር ከመሆኗ ባሻገር ህገ-ወጥ ስደተኞችንና አዘዋዋሪዎችን ለመቆጣጠርም ተመራጭ ሀገር ነች፡፡ ስለሆነም ትልቅ ሚና መጫወት ይጠበቅባታል ሲሉ አክለዋል፡፡ ዜናው የኦል አፍሪካ ነው፡፡

Thursday, 23 October 2014 09:20

ሰሜን ኮሪያ በቁጥጥ ስር ያዋለቻቸውን አሜሪካዊ መልቀቋን አስታወቀች፡፡

ጥቅምት 13/2007 ዓ.ም

ጂፍሪ ፎል የተለቀቁት ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት በፕሬዝዳንት ኪም ዩንግ ኡን ትዕዛዝ መሰረት መሆኑን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ የ56 ዓመቱ ፎል አስፈላጊውን የህግ ሂደት ተከትሎ ለአሜሪካ ባለስልጣናት ተላልፎ መሰጠቱን የሰሜን ኮሪያ የዜና ወኪል አስታውቋል፡፡ ፎል ወደ ሰሜን ኮሪያ የገቡት ባለፈው ሚያዝያ ወር ሲሆን የተያዙትም በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ የሃይማኖት መፅሃፍ ትተው ከወጡ በኋላ ነው፡፡ ሰሜን ኮሪያ ውስጥ ሃይማኖት ለመስበክ መግባት በወንጀል ድርጊት ያስቀጣል፡፡ የፎል ቤተሰቦች ግን ግለሰቡ ለዚሁ ተግባር ወደ ሰሜን ኮሪያ አለማቅናታቸውን አስተባብለዋለ፡፡ ዘገባው የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ነው፡፡

Tuesday, 21 October 2014 10:09

የቻይና መንግሥት በኢቦላ ለተጠቁ ሶስት የአፍሪካ ሀገራት እርዳታ አደረገች፡፡

ጥቅምት 11/2006 ዓ.ም

የዓለም የምግብ ፕሮግራም እያደረገ ያለውን ስርጭቱ የተዛመተባቸውን እና በርካቶች እየሞቱበት ያለው የኦቦላ ቫይረስ ለመከላከልና አስተማማኝ የጤና ክትትልና ህዝቦችን የመርዳት ተግባሩን ያግዝለታል የተባለለትን የገንዘብ እርዳታ ነው የቻይና መንግሥት አደረገች የተባለው፡፡

ጊኒ፣ ላይቤሪያ እና ሴራሊዮን የ6 ሚሊዮን ዶላር እርዳታን ከቻይና መንግሥት ያገኙ ሀገራት ሲሆኑ እኩልም ይካፈላሉ ተብሏል፡፡

ሶስቱ ሀገራት በኢቦላ ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቁና ህዝቦቹም የምግብ እጥረት እያጋጠማቸው በመሆኑ መመረጣቸው ተነግሯል፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለአንድ ወር ያህል የሚቆይ ከ300,000 በላይ ህዝቦችን ሊመግብ የሚች ገንዘብ ማግኘታቸውን የተናገሩ ሲሆን ሩዝ እና የመሳሰሉትን የምግብ አይነቶችን እንደሚገዙ ተናግረዋል፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የምዕራብ አፍሪካ ክልላዊ ዳይሬክተር ዴኒስ ብራውን የቻይናን መንግሥት የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦችን እናመሰግናለን፤ በአስቸጋሪ ጊዜ ላይ በነበርንበት ወቅት ላይ ነው ይህን እርዳታ ያደረጉልን ብለዋል ሲል የቻይና ዴይሊ ድረ-ገፅ አስነብቧል፡፡

Monday, 20 October 2014 13:06

ኬንያን ከሶማሊያ በሚያገናኛት ድንበር ላይ ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ የኬንያን ፖሊስ ሃይል መሪ መግደሉ ተነገረ፡፡

ጥቅምት 10/2007 ዓ.ም

በሊቦይ ድንበር መሪው በተደጋጋሚ በጥይት መደብደቡ የተገለፀ ሲሆን ወደቤቱ እያቀና ባለበት ሰዓት መሆኑም ታውቋል፡፡

አንዳንድ እማኞችን ይዘናል የሚሉ ምንጮች እንደሚሉት፤ ጥቃት አድራሾቹ ተኩስ ከመክፈታቸው በፊት አራት ሆነው የፖሊስ መሪውን ይከታተሉ ነበር፡፡

ከሶማሊያ 18 ኪ.ሜ በምዕራብ በኩል ርቆ የሚገኘው ሊቦይ በእጅጉ የተጨናነቀ የገበያ ማዕከል ነው፡፡ ከሌሎች ከተሞች አንፃር ሲታይም ብዙ ጥቃትና ሽብር የማይከሰትበት ነው፡፡ የታጣቂዎቹ ማንነት እስካሁን በውል ባይታወቅም ክትትል እንደሚደረግባቸውና ለፍርድ እንደሚቀርቡም የኬንያ የፀጥታ ሃይል ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡ ዘገባው የደይሊ ኔሽን ነው፡፡

Friday, 17 October 2014 11:51

ቻይና ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመጣመር ፅንፈኝነትን እና አሸባሪነትን ለመግታት ተስማማች፡፡

ጥቅምት 07/2007 ዓ.ም

የትብብር ስምምነቱ የተጠናከረ ህብረት በመፍጠር ታጣቂ ቡድኖችን ለማዳከም ያለመ ነው ተብሏል፡፡ የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር  ከአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ከሆኑ ማኑኤል ባሩሶ እና ከአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቫን ሮምፑይ ጋር መወያየታቸው ነው የተነገረው፡፡ በጣሊያኗ ሚላን እየተካሄደው ባለው በዚሁ ውይይት የመካከለኛው ምስራቅ እና ወቅታዊ ሁኔታዎች በዋናነት ተነስተዋል፡፡ በተጨማሪም ዩክሬንን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርህ መሰረት ወደ መረጋጋት መምጣት እንድትችል የአውሮፓ ህብረት መሪዎች እና የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስት የትብብር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ዘገባው የቢቢሲ ነው፡

Tuesday, 14 October 2014 10:49

በሞቃዲሾ ከተማ በመኪና ላይ የተጠመደ ቦንብ ፈንድቶ 20 ሰዎች ህይወታቸው አለፈ፡፡

መስከረም 04/2007 ዓ.ም

በሶማሊያ ከተማ በሞቃዲሾ በርካቶችን ከሚያስተናግዱ ካፌዎች አጠገብ በቆመ መኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ 20 ሰዎችን ለሞት፤ ብዙዎችን ለጉዳት መዳረጉን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ተቋማት ወቀሳ ተሰንዝሯል፡፡

በትናንትናው ዕለት የሀገሪቱ መንግሥት፣ የተ.መ.ድ እና የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች በጥምረት ወቀሳቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ጥቃቱን የከፋ ጭካኔ የታየበት ብለውታል፡፡ ለድርጊቱ ተወቃሽ /ተጠያቂ/ የሚሆነውም የአልሸባብ ቡድን እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡

በተለይም ቡድኑ ተደጋጋሚ ችግር እየፈጠረ ያለው በንፁሃን ዜጎች ላይ መሆኑና ዓላማ የለሽ ተግባር ሊባል የሚችል ስለሆነ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሁኔታው እየተባባሰ ነው፡፡ ለዚህ ሀገሪቱንም ሆነ ጎረቤት ሀገራትን ስጋት ላይ ለጣለ ቡድንም ዓለም አቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልና የሀገሪቱም መንግሥት ታጣቂዎቹን ለመቆጣጠር ከበድ ያለ እንቅስቃሴ እንደሚጀምር ፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ መሃመድ ገልፀዋል፡፡ ዘገባው የደይሊ ኒውስ ነው፡፡

Tuesday, 14 October 2014 10:49

በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት የህክምና ተመራማሪዎች ኢቦላን በሁለት ደቂቃ የሚገድል አልትራቫዮሌት ጨረር ሮቦት ማግኘታቸው ተሰምቷል፡፡

መስከረም 04/2007 ዓ.ም

የዚህ የቴክኖሎጂ ግኝት መፍትሄ ላልተገኘለት ኢቦላ መልካም የሚባል ዜና እንደሆነ ታውቋል፡፡ መሳሪያው በተቀመጠበት ቦታ ሆኖ የኢቦላ ቫይረስ እየፈለገ የማጥፋት አቅም እንዳለው ነው የተነገረው፡፡ መሳሪያውን ለመግዛት አንድ መቶ ሺህ የአሜሪካ ዶላር ሲያስፈልግ የመሳሪያውም ስም ጀኔክስ ጃርም ዛቢንግ ሮቦት የሚል ስም ተሰጥቶታል፡፡ ከሮቦቱ የሚለቀቀው ጨረር የኢቦላ ቫይረስ የተጋነነባቸውን ቅንጣቶች በማጥፋት ቫይረሱን እንደሚያጠፋ ነው የተነገረው፡፡ እስካሁን ባለው ሂደት 250 ሆስፒታሎች መሳሪያውን ለአገልግሎት እንዳዋሉ ናቹራል  ኒውስ ነው የዘገበው፡፡

Monday, 13 October 2014 09:51

ቱርክ አሜሪካ በቀጠናው ስጋትነቱ እያየለ የመጣውን IS ለመዋጋት የጦር አካባቢዋን እንድትጠቀም መስማማቱ ተነገረ፡፡

ጥቅምት 03/2007 ዓ.ም

በደቡባዊ ቱርክ ያለውን ቦታ ቱርክ መፍቀዷን ሱዛን ራይዝ አድንቀዋል፡፡ ቱርክ IS የሚገኝባቸው የሶሪያ እና የኢራቅ ድንበሮችን ታጋራለች፡፡

በቱርክ ድንበር አቅራቢያ በIS እና በኩርድ ሃይሎች እየተደረገ ያለው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ዘገባዎች አመላክተዋል፡፡

በኮባኒ እየተደረገ ባለው ጦርነት 200,000 የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ድንበር አቋርጠው ወደ ቱርክ ተሰደዋል፡፡ ዜናው የቢቢሲ ነው፡፡

Friday, 10 October 2014 10:14

ኡራጓይ የመጀመሪያ የሆኑ እና ወደ ሀገሯ የመጡ የሶሪያ ስደተኞችን ተቀብላለች፡፡

መስከረም 30/2007 ዓ.ም

42 የሚጠጉት ስደተኞች በአምስት የቤተሰብ አባላት የተከፈሉ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ከሊባኖስ የመጡትን ስደተኞች የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆሴ ሙኪካኦ ተቀብለውም አነጋግረዋል፡፡ ስደተኞቹ ለሁለት ወራት ያህል በሚኖራቸው ቆይታ ሙሉ ወጪዎቻቸው ተችሎ ከኡራጓይ ዋና ከተማ በቅርበት በምትገኘው ሞንቴቪዲዮ የስፓኒሽ ቋንቋ እና የሀገሪቱን ባህል እንደሚማሩም ተነግሯል፡፡ ኡራጓይ የተቀበለቻቸውን ስደተኖች ለስራ ብቁ የሆኑትን ወደ ስራ ለማስገባት እና ህፃናቱን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ማቀዷ የታወቀ ሲሆን ለዚህም የሁለት ዓመት ወጪው ሶስት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደምታወጣ ተገልጧል፡፡ ከሶሪያ የሚመጡ ስደተኞችን የደቡብ አሜሪካ ሀገራት እየተቀበሉ ቢገኙም ኡራጓይ ግን የስደተኞቹን ወጪ በመሸፈን በቀበሏ የመጀመሪያ ሀገር አድርጓታል፡፡ ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

Thursday, 09 October 2014 14:54

ከፈረንጆቹ ሚያዚያ ጀምሮ በዩክሬን ቀውስ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 3,660 መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ፡፡

መስከረም 29/2007 ዓ.ም

ከሚያዝያ አጋማሽ እስከ ማክሰኞ በነበረው ጊዜ ህይወታቸውን ካጡት 3,660 በተጨማሪ 8,756 የሚሆኑት ሰዎች በምስራቅ ዩክሬን ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቢሮ በትላንትናው ዕለት ባወጣው ወርሃዊ ሪፖርት ነው ጉዳዩን ያስታወቀው፡፡

በአማፂያኑ እና በዩክሬን መንግሥት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ በኋላም ቢሆን ቀውሱ የተረጋጋ ቢመስልም ግጭቶች ነበሩ ያለው ሪፖርቱ ሰዎች በዚሁ ቀውስ ሂወታቸውን እንዳጡ አትቷል፡፡ ዘገባው የYahoo News ነው፡፡ 

Thursday, 09 October 2014 14:53

በማሊ በተለይ በሀገሪቱ በሰሜን ክፍል ያሉ ታጣቂዎችን ለመዋጋት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወታደሮች እንዲላኩ ተጠይቀዋል፡፡

መስከረም 29/2007 ዓ.ም

የማሊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብሉላዬ ዲዮብ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በቅርቡ በተ.መ.ድ ሰላም አስከባሪዎች ላይ የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ አፋጣኝ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ተወስኗል፡፡

በታጣቂዎቹ ቀደም ባለው ጊዜ ከኒጀር የመጡ 9 ሰላም አስከባሪዎች ተገድለው የነበረ ሲሆን ማክሰኞ እለት ደግሞ አንድ ሴኔጋላዊ ሰላም አስከባሪ ህይወቱን አጥቷል፡፡

የተ.መ.ድ ሰላም ማስከበር ቡድን ሃላፊ እንዳሉት በማሊ ያለው ወታደራዊ ሃይል የፈረንሳይ ወታደሮች በመልቀቃቸው የተፈጠረውን ክፍተት መሸፈን አልቻለም፡፡

ምንጮች እንዳመለከቱት እስካሁን እ.ኤ.አ በ2013 ተልዕኮውን ለማስፈፀም ወታደሮች ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ 31 ሰላም አስከባሪዎች ሞተዋል፤ 91 የሚሆኑት ቆስለዋል፡፡ ዘገባው የBBC ነው፡፡

Tuesday, 07 October 2014 09:14

የላይቤሪያ የህትመት ሚዲያ ህብረት የሀገሪቱ መንግሥት በኦቦላ በሽታ ላይ የሚሰሩ ዘገባዎችን እያገደ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

መስከረም 27/2007 ዓ.ም

በሱዳን በኢቦላ ዙሪያ የሚሰሩ ዘገባዎች ይታገዱ መባሉን የሚያመላከተው ዘገባ መውጣቱን ተከትሎ፤ የላይቤሪያ የህትመት ሚዲያ ህብረትም ተመሳሳይ ችግር መኖሩን አመላክቷል፡፡ የህብረቱ አባላት መንግሥት በሽታውን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ከማጠናከር ይልቅ ዘገባዎችን ማገዱ አግባብ አይደለም ሲሉ ወቀሳቸውን እየሰነዘሩ ነው፡፡

የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ በዚህ ዙሪያ የሚተላለፉ ጉዳዮች መስመር እየሳቱ ነው የሚል አስተያየት አለው፡፡ ለማገገሚያነት በተሰሩ የጤና ማዕከላት ውስጥ የሚነሱ ፎቶግራፎች፣ የሚሰሩ ቃለ-መጠይቆችና ተያያዥ ጉዳዮች የህሙማንን መብት መጋፋት እንደሆነም እየተነገረ ነው፡፡ የሚዲያዎችን ነፃነት የሚጋፉ ተግባራት ተመልስው መምጣታቸው የሀገሪቱን ዴሞክሲያዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው መባሉን VOA ዘግቧል፡፡

Tuesday, 07 October 2014 09:14

የእስራኤል ታጣቂ ቡድን የሆነ እና በአንፃሩ አይ ኤስ ተብሎ የሚጠራው ቡድን የሽብር ጥቃቱን ለማስፋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተነገረ፡፡

መስከረም 27/2007 ዓ.ም

የአሸባሪ ቡድኑ አባላት የሆኑ ኮማንዶዎቹን በስደተኞች ስም ወደ ምዕራብ አውሮፓ በመላክ የሽብር ጥቃት ለማድረስ እያሴረ መሆኑን ጀርመን የተናገረች ነው፡፡ አራት አባላት ያሉት የሽብር ቡድን በሶሪያና ቱርክ ድንበር ሰርጎ በመግባት እና በተጭበረበረ የጉዞ ሰነድ ወደተለያዩ የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ለመግባት ማቀዱ ነው የታወቀው፡፡ የሽብር ቡድኑም ጀርመን ለኩርድ ወታደሮች ድጋፍ ማድረጓን ተከትሎ የሽብር ጥቃት ለመሰንዘር አስቧል፡፡ ምንም እንኳን ጀርመን እንዲህ ብትልም የአሜሪካ የደህንነት አባላት እንዳስታወቁት ከሆነ በአየር ማረፊያዎች እጅግ ጥብቅ ቁጥጥር በመኖሩ አሸባሪዎች አውሮፕላኖችን እንደማይጠቀሙ ተናግረዋል፡፡

የተረጋገጠ የሽብር ጥቃት ፍንጭ ባይኖርም ጀርመን የአሸባሪዎች ቀጣይ የጥቃት ኢላማ ናት ሲሉ የጀርመን የሀገር አስተዳደር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ተናግረዋል፡፡ ዘገባው የሮይተርስ ነው፡፡

Thursday, 02 October 2014 12:23

የቻይናዋ ከፊል ራስ ገዝ መስተዳድር ከተማ የሆንግ ኮንግ ህዝብ የከተማይቱን አስተዳደር በመቃወም የጀመረውን ሰልፍ እንደቀጠለ ነው፡

መስከረም 22/2007 ዓ.ም

የከተማው ህዝብ ባለፈው እሁድ የጀመረውን የተቃውሞ ሰልፍ እንዲያበቃ የከተማው አስተዳደርና የቻይና ማዕከላዊ መንግሥት ቢጠይቁም ሰልፉ አለመቋረጡን ተናግረዋል፡፡ የፀጥታ አስከባሪዎች አስለቃሽ ጋዝ በመጠቀም ሰልፈኛውን ለመበተን ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካም መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ የሰልፈኞቹ መልዕክት በሀገሪቱ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የሆንግ ኮንግ  ዋና አስተዳዳሪ በነፃነት መምረጥ በሚችሉበት ዙሪያ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ምንም እንኳን ሰልፈኞችን ለመበተን የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም የተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪዎች እንዳሉት የሆንግ ኮንግ ዝናባማና ነፋሻማ አየርን በመቋቋም በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የከተማይቱ አደባባይ ላይ ተገኝተዋል፡፡ ሰልፉ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ስልጣን ከያዘበት 65 ዓመት ክብረ በዓል ጋር መገጣጠሙን ሮይተርስ ነው የዘገበው፡፡

Thursday, 02 October 2014 12:19

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቀድሞ ተዋጊዎች በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ለከፋ ረሀብ እየተጋለጡ ነው ተባለ፡፡

መስከረም 22/2007 ዓ.ም

ከ100 በላይ የሚሆኑና ቀድመው በውጊያ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ወታደሮች በዚሁ በገጠማቸው ረሀብ ምክንያት ህይወታቸውን እያጡ ነው፤ ቤተሰቦቻቸውም ተመሳሳዩ እጣ ደርሷቸዋል፡፡

የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት እንዳመላከተው ባለፈው ዓመት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜን ምዕራብ ክፍል በሚገኘው ብዙ ትኩረት በማይሰጠው ካምፕ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡ ይህም የተደረገው እጅ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው፡፡

የሚላክላቸው ምግብ ሊዳረስ የሚችል አይደለም የተባለ ሲሆን የጤና አገልግሎቱንም በበቂ ሁኔታ ማግኘት አልቻሉም፡፡ አንዳንዶቹም በአካባቢው ካሉ ገበሬዎች እህል መስረቅ ጀምረዋል፡፡ የሀገሪቱ ወታደራዊ ሃይል ጉዳዩን አጣራዋለሁ ያለ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ተጠይቋል፡፡ ዜናው የቢቢሲ ነው፡፡

Tuesday, 30 September 2014 09:12

በአልጄሪያ ፈረንሳያዊው ቱሪስት መገደሉን ተከትሎ የቱሪዝም ዘርፉ ሊጎዳ እንደሚችል ተነገረ፡፡

መስከረም 20/2007 ዓ.ም

ባለፈው ሳምንት በሀገር ውስጥ ታጣቂዎች በፈረንሳዩ ቱሪስት ላይ የተደረገው አፈና እና ግድያ ከአይ ኤስ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል፡፡

ይህም የሰሜን አፍሪካ ሀገራትን ያሰጋ ሲሆን የቱሪዝም ኢንዱስትሪውም ተቀዛቅዟል፡፡

በአልጄሪያ ደቡብ ክፍል ያሉት በርካታ የቱሪዝም ኤጀንሲዎች ባቀረቡት ሪፖርት መሰረት በርካታ ጎብኚዎች ወደ ሰሀራ በረሀ ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ ሰርዘዋል፡፡ ኤጀንሲዎቹ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ለውጥ ማምጣት የሚችለውን ቱሪዝምን ለማጠናከር ሀገሪቱ ምቹና ሰላማዊ መሆኗ በስፋት ሊቀሰቀስ ይገባል እያሉ ነው፡፡

የ55 ዓመቱ ፈረንሳያዊ ጎብኚ ጉዳይ ግን በእቅዱ ላይ ከፍተኛ የሆነ እንቅፋት ሆኗል፡፡

አልጄሪያ መሰል ተግባራትን ለመከላከል ተጨማሪ ወታደራዊ ሀይል ያሰማራች ሲሆን ቱሪስቶችም መረጃዎችን አሟልተው የሚገኙበትና እነርሱም በግልፅ ያሉበትን ሁኔታ የሚናሩበት መንገድ ምቹ ሆኗል፡፡ ዜናው የኦል አፍሪካ ነው፡፡