አለም አቀፍ ዜናዎች (169)

Wednesday, 02 September 2015 09:21

ኬንያ አበረታች መድኃኒት የሚወስዱ ስፖርተኞችን በወንጀል የሚያስጠይቅ ህግ ተግባራዊ ልታደርግ መሆኑን የኬንያው ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ተናገሩ፡፡

ነሐሴ 27/2007 ዓ.ም

ሰሞኑን በቤጂንግ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የነበረው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በአንደኝነት የፈፀመችው የምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኬንያ ከአበረታች መድኃኒት ቅሌት ጋር በተገናኘ ስሟ በተደጋጋሚ በዓለም መድረክ መነሳቱ የሀገሪቱን ገፅታ እያበላሸ መሆኑን፤ ለዚህ ችግር አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትም አዲስ ህግ ተግባራዊ እንደሚደረግ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

ኬንያ አመርቂ ውጤት ባስመዘገበችበት በ15ኛው የቤጅንግ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ካሳተፈቻቸው አትሌቶች መካከል ሁለት አትሌቶቿ የአበረታች መድኃኒት ተጠቅመው መገኘታቸው አይዘነጋም፡፡

ኬንያ ከአበረታች መድኃኒት ጋር በተገናኘ ስሟ በተደጋጋሚ መነሳቱን መንግሥት በቸልታ አይመለከተውም ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በአበረታች መድኃኒት ቅሌት ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ ስፖርተኞች፣ የህክምና ባለሞያዎችን ጨምሮ የስፖርተኞች ወኪሎች በህግ እንዲጠየቁ ከተደረጉ በኋላ ተገቢውን ቅጣት ያገኛሉ ብለዋል፡፡ ዘገባው የቫንጋርድ ድረ-ገፅ ነው፡፡

Wednesday, 15 July 2015 09:50

የሩዋንዳ ህዝቦች ፓርላማ የምርጫ ህጉ እንዲስተካከል ጠየቀ፡፡

ሐምሌ 08/2007 ዓ.ም

ከ3.7 ሚሊዮን በላይ ሩዋንዳዊያን ትናንት በፓርላማው ተገኝተው የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው የስልጣን ገደብ ይነሳ ሲሉ ድምፅ መስጠታቸው ነው የተነገረው፡፡

ፕሬዝዳንቱ ፖልካጋሜ ለ2017ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዳግም እንዳይወዳደሩ የሚከለክለውን ህግ ለማሻሻል አልያም ለመለወጥ ህዝብ ድምፅ ይስጥበት ያሉ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት ሚሊዮኖች ፕሬዝዳንቱ ዳግም ሀገሪቱን እንዲመሩ እና በምርጫም እንዲወዳደሩ ፈልገዋል ተብሏል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ይህ የህዝቤ ውሳኔ ነው፤ እኔ ህግን የመለወጥ እና በራሴ ህግ የመመራት ስልጣን የለኝም፤ አሁንም የህዝቤን ድምፅ አከብራለሁ ብለዋል፡፡

ቀኝ ዘመም የፖለቲካ ቡድኖች ደግሞ የሩዋንዳን የህግ አውጪዎች የወነጀሉ ሲሆን ዝም ማለቱም መልካም አይደለም ብለዋል፡፡ ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

Wednesday, 17 June 2015 12:55

የሶማሊያ ተማሪዎች ከ25 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሔራዊ ፈተና ተቀመጡ፡፡

ሰኔ 10/2007 ዓ.ም

7,000 ተማሪዎች ማጠቃለያ ፈተናቸውን መውሰድ መጀመራቸው ሀገሪቱ ካለችበት የተሻለ ሁኔታ ጋር የሚያያዝ ነው ሲል ዘገባው ገልጧል፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አጠቃላይ ፈተና ለሚወስዱበት ታላቅ ቀን መብቃታችን ስኬት ነው፤ በፈተናው ስኬታማ እንድትሆኑ እመኛለሁ ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

የውስጥ ፀጥታ ሃላፊው አብዱራዛክ ኦማር ሙሀመድ እንዳሉት ከሆነ ፈተናው በሚሰጥባቸው ጣቢያዎች ምንም አይነት የሽብር ጥቃት እንዳይፈፀም ክትትል እየተደረገ ነው፡፡

እ.ኤ.አ ከ1991 ወዲህ በሀገሪቱ ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና ሲሰጥ ይህ የመጀመሪያው ነው በማለት ዘገባውን ያስነበበው ዥንዋ ነው፡፡

Monday, 18 May 2015 14:10

ኢኳደር በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 647 ሺ 250 ችግኞችን ተከለች፡፡

ግንቦት 10/2007 ዓ.ም

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ራፋኤል እንዳሉት ከሆነ የተለያዩ አይነት የዛፍ ችግኞች ተተክለዋል፤ የጊነስ ሪከርድ መሰበሩንም ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቱ የአካባቢ ሚኒስቴር እንዳሉት ከሆነ 44ሺ 883 ሰዎች በችግኝ ተከላው ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በአጠቃላይ ከ2,000 ሄክታር መሬት በችግኞች ተሸፍኗል ሲል በትዊተር ገፁ ገልጧል፡፡

ችግኞቹ ሲፀድቁ በአካባቢያዊ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ አዎንታዊ ለውጥን ያመጣሉ ተብሏል፡፡ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ክብረ-ወሰንን በዓለም አቀፉ የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ማስፈር የቻለችው ፊሊፒንስ ነበረች ሲል አስታውሶ የዘገበው ፕሬስ ቲቪ ነው፡፡

Monday, 18 May 2015 14:01

በትምህርት ቤቶች የሞባይል ስልክ መጠቀምን መከልከል በተማሪዎች ውጤት ላይ በጎ የሆነ ለውጥ ማምጣቱን በእንግሊዝ የተደረገ ጥናት ጠቆመ፡፡

ግንቦት 10/2007 ዓ.ም

በ4 የእንግሊዝ ከተሞች በተሰበሰበው ዳታ አማካኝነት በተደረገው ጥናት መሰረት የተማሪዎች ውጤት በ6 በመቶ አድጓል፡፡ ሊዊስ ፍሊፒስ እና ሪቻርድ መርፊ በጥናቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን የሞባይል ስልኮች በተማሪዎች ላይ የውጤት መቀነስ፣ በዙሪያቸው ያሉትን ሰዎች በመረበሽ ህይወታቸው ይረበሽ ነበር ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በጥናቱ ውስጥ የተካተቱት ተማሪዎች እድሜ ከ11-16 ነው፡፡

ለንደን School of Economics ጥናቱን ሲያጠቃልል እንደተነተነው ከሆነ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን ውጤታማ መሆን የሚፈልጉ ከሆነ የሞባይል ስልክ ወደ ት/ቤት ይዘው እንዳይመጡ መከልከል አለበት ብለዋል፡፡ ዘገባው የፕሬስ ቲቪ ነው፡፡

Monday, 18 May 2015 13:59

ደቡብ አፍሪካ ከ400 በላይ የሞዛምቢክ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ላከች፡፡

ግንቦት 10/2007 ዓ.ም

በሀገሪቱ በደርባን እና ጆሃንስበርግ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ ነው ወደ ሀገራቸው የተመለሱት፡፡ ስደተኞች ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የላቸውም፡፡

በደቡብ አፍሪካ ያሉት ስርዓጥ ዜጎች ምክንያት የሚያደርጉት የውጭ ሀገር ዜጎችን ሆኗል፡፡ በሀገሪቱ የስራ አጥ ቁጥር 24 በመቶ ነው፡፡ የሞዛምቢክ መንግሥት በበኩሉ በደቡብ አፍሪካ እርምጃ መገረሙን አስታውቋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ለመወያየት አቅደን ነበር ነገር ግን ዜጎች ታስረዋል በማለት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር Oldemiro Baloi ገልፀዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ በተነሳው የውጭ ዜጎችን ጥላቻ ግጭት ከሞቱት 7 ሰዎች መካከል አንዱ ሞዛምቢካዊ ነው፡፡

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት መግለጫ እንደሚያመለክተው ከሆነ ከሚያዝያ ጀምሮ 3,900 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ከነዚህ መካከል 1,650 የሚሆኑት ህገ-ወጥ ስደተኞች ናቸው ብሏል፡፡ ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

Monday, 06 April 2015 12:11

የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የቦኮሃራም የሽብር ተግባር ላይ ለመምከር ቀጠሮ መያዛቸው ተገለፀ፡፡

መጋቢት 28/2007 ዓ.ም

በማዕከላዊና በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ያሉ መሪዎች የቦኮሃራምን ጥቃት /የሽብር ተግባር/ በመከላከል ላይ ለመምከር ቀጠሮ የያዙት በፈረንጆቹ ሚያዝያ 8 ላይ ነው፡፡ በትናንትናው ዕለት ስብሰባውን በጥምረት የሚያዘጋጁት ኢኮዋስ (ECOWAS) እና ኢካሳ (ECCAS) እንዳስታወቁት መሪዎቹ በተጠቀሰው ቀን ለመመካከር የሚገናኙት በኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቦ ነው፡፡

የቀድሞው የወታደራዊ ሃይል መሪ የነበሩት ሙሀመድ ቡሃሪ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸው ከተሰማ በኋላ ቀጠሮ የተያዘለት የመጀመሪያው ስብሰባ ነው፡፡ ምንጮች አዲስ የተመረጡት ፕሬዝዳንት ቡሃሪ ቃለ-መሃላቸውን ይፈፅማሉ ተብሎ የሚጠበቀው በፈረንጆቹ ግንቦት 29 መሆኑን ያመላከቱ ሲሆን በቦኮሃራም ላይ ለመምከር በታሰበው በዚሁ ስብሰባ ላይ መገኘታቸውን በተመለከተ የተረጋገጠ ነገር አለመኖሩን ጠቁመዋል ሲል የዘገበው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ነው፡፡

Thursday, 19 March 2015 10:38

የአሜሪካው መከላከያ መስሪያ ቤት የአልሸባብ መሪ የሆነውን አዳን ጋራርን በከፈተው የጥቃት ዘመቻ መግደሉን አስታወቀ፡፡

መጋቢት 10/2007 ዓ.ም

ፔንታጎን እንዳለው ታጣቂው እሮብ እለት በደቡብ ሶማሊያ ሊመታ ችሏል፡፡

እ.ኤ.አ. 2013 ላይ በኬንያ ዌስትጌት የገበያ ማዕከል 67 ሰዎችን ለሞት በዳረገው ጥቃት ጋራር ተጠርጣሪው ነው፡፡

ሰውየው አልሸባብን በማቀናጀት በኩል ቁልፍ ሚና የሚጫወት ነው የተባለ ሲሆን፤ በቅርቡም ሌላ ተልዕኮ በማቀናጀት ላይ እንደነበር ተገምቷል፡፡

በሶማሊያና በሌሎች ጎረቤት ሃገራት ስጋት የሆነውን የአልሸባብ  ቡድን ለማስወገድ እየተረባረበ ካለው የአፍሪካ ህብረት ጋር አሜሪካም ማበር የጀመረችው በፈረንጆች 2011 ላይ ነው፡፡ የታጣቂውጋራር ሞት ይፋ ከመደረጉ ከሰዓታት ቀድሞ አልሸባብ በሰሜን ምስራቅ ኬንያ 4 ሰዎችን ገድሎ የነበረ ሲሆን ታጣቂ ቡድኑ ኬንያ በህብረቱ እንቅስቃሴ ውስጥ ለፈጸመችው አልሸባብን የመጣል እንቅስቃሴ ቅጣት ይገባታል ሲል መዛቱን አሶሼትድ ፕሬስ  ዘገቧል፡፡ 

Wednesday, 18 March 2015 12:36

ኢንዶኔዢያ በቅርቡ ከ30 ሀገራት ለሚመጡ ጎብኚዎች ያለቪዛ ሀገሪቱን እንዲጎበኙ እንደምትፈቅድ ገለፀች፡፡

መጋቢት 09/2007 ዓ.ም

ሀገሪቱ ካጋጠማት የኢኮኖሚ እድገት መቀዛቀዝ ጋር በተያያዘ የውጭ ሀገር ባለሃብቶች እና ጎብኝዎችን በመሳብ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ እንዲረዳት በማሰብ መሆኑን የኤምሬትስ 24/7 ዘገባ አመላክቷል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ሀገሪቱ ከ15 ሀገራት የሚመጡ ጎብኚዎች ያለቪዛ ይገባሉ፤ ከነዚህ ዜጎች መካከል አብዛኛዎቹ የኤዥያ ሀገራት ዜጎች መሆናቸው ተገልጧል፡፡

ከ30 ሀገራት መካከል የአሜሪካ፣ የአውሮፓ፣ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ቱሪስቶች ይካተቱበታል እየተባለ ይገኛል፡፡

ወደ ሀገራችን የሚመጡ ሰዎች ከዚህ በኋላ ስለቪዛ ጉዳይ መጨነቅ የለባቸውም ሲል የሀገሪቱ መንግሥት ገልጧል፡፡

በዚህ እቅድ ሀገሪቱ ከቱሪስቶች ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የማግኘት እቅድ ይዛለች፡፡ አዲሱ አሰራር በሚቀጥለው ወር ስራ ላይ መዋል ይጀምራል ሲል ኤምሬትስ 24/7 ዘግቧል፡፡

Thursday, 12 March 2015 12:10

የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣናት ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ጋር በተያያዘ ሁለት የውጭ ሀገር ዜጎችንና አንድ የሀገሪቱን ዜጋ አንገት ቀልተው ገደሉ፡፡

መጋቢት 03/2007 ዓ.ም

የሳውዲ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳሉት ሀሙድ ሀጁሪ ከየመን እንዲሁም መሀመድ ከዛው ከሳውዲ የተያዙት በደቡብ ምዕራብ ግዛት Jizan ነው፡፡ በተያያዘ ፋዲ አብዱልራዛቅ የተባለው የሶሪያ ዜጋ በሰሜን ግዛት ጃውፍ ተይዟል፡፡

በዚህ ዓመት ብቻ ተመሳሳዩ እርምጃ የተወሰደባቸው ብዙ በመሆናቸው ህገ-ወጥ የእፅ ዝውውሩም እየቀነሰ ይገኛል ሲሉ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

የሀገሪቱ ባለስልጣናት በበኩላቸው መንግሥት በሳውዲ ሰላም እንዲሰፍን የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅና ፍትህ እንዳይጓደል በሚል የማያዳግም እርምጃ መውሰዱ ይቀጥላል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

ፍርዱ በተለያዩ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ እየተተቸ ነው በሳውዲ አረቢያ አስገድዶ መድፈር፣ የግድያ ወንጀል፣ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር የታጣቂዎች እና እምነት መለወጥ ሙሉ ለሙሉ የሞት ቅጣትን የሚያስወስኑ ናቸው ዘገባው የያሁ ኒውስ ነው፡፡

Thursday, 12 March 2015 12:03

አለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም IMF 17.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለዩክሬን መፍቀዱ ተነገረ፡፡

መጋቢት 03/2007 ዓ.ም

የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ማኔጂንግደ ዳይሬክተር ክርስስቲን ላጋርድ በትናትንው ዕለት በሰጡት መግለጫ አዲሱ የተቋሙ ፕሮግራም ተጨማሪ እርዳታ፣ ግዜ እንዲሁም ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን በጦርነት ለተጎዳችው ዩክሬን ይሰጣል ብለዋል፡፡

ቀደም ብሎ የዩክሬን የገንዘብ ሚኒስትር ናታሊ ጃሬስኮ ኬቭ በቅርብ ቀናት ውስጥ $ 5 billion ያህል ብድር ትፈልጋለች ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ዘገባው የዩክሬን ፕሬዚዳንት የሆኑት ፔትሮ ፓርሼንኮ በግብርና ሌሎች ወጪዎች ላይ የዋጋ ማስተካከያ/ ቅነሳ ለማድረግ መስማማታቸውን ይፋ እንዳደረጉም አስታውሷል፡፡  

እንደ ተ.መ.ድ. ሪፖርት በምስራቅ ዩክሬን በነበረው ግጭት ከ6ሺ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ 1.5 ሚሊየን የሚሆኑት ደግ መኖሪያቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል ዘገባው የዩሮ ኒውስ ነው፡፡ 

Thursday, 12 March 2015 11:53

ሶማሌ ላንድ በቅርቡ ለማካሄድ ያሰበችውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማራዘሟ ተነገረ፡፡

መጋቢት 03/2007 ዓ.ም

የሃገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን እንዳስታወቀው፤ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ለቀጣይ ዘጠኝ ወራት እንዲራዘመ ውሳኔ ማስተላለፉን አመላክቷል፡፡

በሶማሊ ላንድ ሊካሄድ የታሰበው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በሊለንዮ መንግስትና በተቃዋሚዎች መካከል ውዝግጅ መፍጠሩን ያመላከተው የሃገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን፤ ምርጫው የተራዘመበት ዋነኛ ምክንያት ከዚሁ ጋር በተገናኘ የተፈጠሩ ችግሮችን ፈር ለማስያዝ ነው ብሏል፡፡

ኮሚሽኑ ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ምዝገባን ከስድት ወራት በኋላ መካሄድ እንደሚጀምር ጠቁሟል፡፡ ሃገሪቱ ከዚህ ቀደም የተሳካና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄዷን በማስታወስ የዘገበው ኦል አፍሪካ ድረገጽ ነው፡፡

በአፍሪካ ህብረት ጥምር ጦር ድጋፍ የሚደረግለት የሶማሊ መንግሥት ጦር ኃይል አልሸባብ ላይ በከፈተው አዲስ ዘመቻ በቡድኑ ይዞታ ስር የሚገኙ አካባቢዎችን ማስለቀቁ ተሰማ፡፡ የሶማሊያ ጦር ኃይል ባሳልፈነው ሰኞ አልሸባብ ላይ በከፈተው ዘመቻ ጋዱድ የተባለውን የአልሸባብ ቁልፍ ይዘት በቁጥጥሩ ስር ማዋል እንደቻለ ተነግሯል፡፡

የሶማሊያ የጸጥታ ኃይሎች አልሸባብ ላይ ባካሄዱት ዘመቻ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የቡድኑ አባላት መማረካቸውን የመንግስት ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ተናግረዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የሶማሊያ መንግሥት አፈቀላጤ በዘመቻው ሶስት የአልሸባብ አባላት መገደላቸውን አስረድተዋል፡፡

የሶማሊያ መንግሥት በቁጥጥሩ ስር ያስገባቸውን ከተሞች ላለፉት 12 ወራት በአልሸባብ ቁጥጥር ስር እንደነበሩ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡ ዘገባው የኦል አፍሪካን ነው፡፡

Monday, 09 March 2015 11:18

በሰሜን ማሊ ኪዳል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መቀመጫ ላይ በደረሰው የሮኬት ጥቃት 3 ሰዎች ህይወታቸውን አጡ፡፡

የካቲት 30/2007 ዓ.ም

ቢቢሲ እንደዘገበው በጥቃቱ ሌሎች 12 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በቦታው ላይ ተደጋጋሚ አደጋ በማድረስ የሚታወቁት እስላማዊ ታጣቂዎች ናቸው የተባለ ሲሆን ሃላፊነቱንም እንወስዳለን ብለዋል፡፡ አንዳንዶቹ ሮኬቶች ኢላማቸውን የሳቱ በመሆናቸው ሁለት ንፁሃን ዜጎችም ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ለዘመናት ከአልቃይዳ ጋር ጥምረት ያለው ታጣቂና የቱዋረግ አማፂያን ወታደራዊ ሃይሉን በሰሜን ማሊ ሲዋጉ ቆይተዋል፡፡ ግጭቱ ይበልጥ እየተባባሰ የመጣው በሳሃራ በረሃ በነፃነት የሚንቀሳቀሰው የጅሃድ አባላት ከተቀላቀሉት በኋላ ነው ተብሏል፡፡ ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

Monday, 09 March 2015 11:09

የመጀሪያው በፀሃይ ብርሃን የሚሰራ የአውሮፕላን በረራ ከዛሬ ጀምሮ በዓለም ዙሪያ ሊደረግ ነው ተባለ፡፡

የካቲት 30/2007 ዓ.ም

በሁለት የሲውዘርላንድ አብራሪዎች አማካኝነት ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አቡዳቢ ከተማ በመነሳት በፀሃይ ብርሃን በሚሰራ አውሮፕላን ለሚቀጥሉት 5 ወራት በመላው ዓለም ለመብረር ይሞክራሉ ተብሏል፡፡

እንደ UPI ዘገባ Solar Impulse-2 የተሰኘው ይህ የፀሃይ ብርሃንን ብቻ የሚጠቀም አውሮፕላን የላይኛው አካሉ የፀሃይን ብርሃን ለመሰብሰብ አመቺ ተደርጎ የተገጠመ ቴክኖሎጂ ያለውና 236 ጫማ ርዝመት ያለው የረዥም ክንፍ ባለቤት ነው፡፡ ቀን የሰበሰበውን የፀሃይ ጉልበት በማጠራቀም  በጨለማ መብረር ይችለልም ተብሏል፡፡ በርትራንድ ፒካርድ እና አንድሬ ፖስቸበርግ በሚያደርጉት በረራ አሜሪካ፣ ህንድን፣ ማይናማርን፣ ቻይናንና አውሮፓን በከፊል ያዳርሳሉ ተብሏል፡፡ ዘገባው UPI ነው፡፡

Friday, 06 March 2015 11:46

በኬንያ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየተበራከተ ነው ተባለ፡፡

የካቲት 27/2007 ዓ.ም

በሀገሪቱ እየተንሰራፋ የሚገኘው የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣት በሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በዜጎች ላይ እያስከተለ ነው ተብሏል፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ ከሃይማኖት ተቋማት፣ የመንግሥት ባለስልጣናት እንዲሁም ከምግባረ ሰናይ ድርጅት የተውጣጡ አመራሮች እንደተናገሩት ከሆነ በተለያዩ ሀገራት የሚመረቱ አደንዛዥ ዕፆችን  ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ኬንያን በስፋት እየተጠቀሙ ነው ብለዋል፡፡ ወደ ሌሎች ሀገራት የሚዘዋወረው ይህ አደንዛዥ ዕፅ በሀገር ውስጥ ገበያ ቀርቦ እየተቸበቸበ በመሆኑ ዜጎች በቀላሉ በዚህ ሱስ እንዲጠቁ እያደረጋቸው ነው ተብሏል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ የፖሊስ አባላትና ፖለቲከኞች እጃቸው በአደንዛዥ ዕፅ ንግድ የተነካካ በመሆኑ ችግሩ እጅግ እየገዘፈ መምጣቱን የኒውስ 24 ዘገባ አመላክቷል፡፡

Wednesday, 04 March 2015 13:38

በቻይና በየዓመቱ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ ተገለፀ፡፡

የካቲት 25/2007 ዓ.ም

እ.ኤ.አ 1983 ላይ የረቀቀውና በፈረንጆቹ 2000 ላይ እንዲከበር ይፋ የሆነው 16ኛው ብሄራዊ የጆሮ ቀን ትናንት በቻይና ተከብሯል፡፡

በፈረንጆቹ ማርች 3 ወይም መጋቢት 3 ዓለም አቀፍ የጆሮ ቀን ሆኖ እንዲከበር የዓለም የጤና ድርጅት 2013 ላይ መወሰኑን ዘገባው አስታውሷል፡፡

ዓላማውም በዋናነት ለጆሮ ጤና ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ ትኩረት የሚሰጥበት /የሚታሰብበት ነው፡፡

እንደ ቻይና የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ሪፖርት በቻይና በየዓመቱ ከ300,000 በላይ የመስማት ችግር የሚያጋጥማቸው ሰዎች ይኖራሉ ለዚህም ምክንያት ነው የተባለው የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን /ድምፅን አለአግባብ መጠቀም ነው መባሉን CCTV ፅፏል፡፡

Wednesday, 04 March 2015 13:21

ሶማሊያ በFBI ግንባር ቀደም ሆነው ከተመዘገቡ ሽብርተኞች አንዱን በቁጥጥር ስር እንዳዋለች አስታወቀች፡፡

የካቲት 25/2007 ዓ.ም

ሊባን ሀጂ የተባለው ትውልደ ሶማሊያዊና በዜግነት አሜሪካዊ ከዚህ ቀደም በዋሽንግተን የታክሲ ሹፌር ሆኖ ይሰራ የነበረ ነው፡፡

ዥንዋ እንደዘገበው ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው ወደ ሞቃዲሾ በመጓዝ ላይ እያለ ነው፤ ተጨማሪ የማጣራት ስራ ሊደረግበትና ለጥያቄ በቁጥጥር ስር እንደዋለ ተገልጧል፡፡

ግለሰቡ እ.ኤ.አ 2012 ላይ አሜሪካን ለቆ የወጣ ሲሆን ይዞ ላስረከበኝም 50,000 የአሜሪካ ዶላር መድቤያለሁ ማለቷን ዘገባው አስታውሷል፡፡ ዘገባው የዥንዋ ነው፡፡

Tuesday, 03 March 2015 15:28

አውስትራሊያ በኢራቅ ያለውን ጦር ለማሰልጠን ተጨማሪ አሰልጣኞችን እንደምትልክ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ አቦት አስታወቁ፡፡

የካቲት 24/2007 ዓ.ም

እሳቸው እንዳሉት ከሆነ ተጨማሪ 300 የጦር አባላት ይልካሉ ተብሏል፡፡ እነዚህ ልዩ የጦር አባላት ቀደም ሲል በኢራቅ ለግዳጅ የሄዱትን 200 ልዩ የጦር ሃይሎችን ይቀላቀላሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ አውስትራሊያ ጦሯን በጥቅምት ወር ወደ ኢራቅ የላከችው IS የተሰኘውን ፅንፈኛ ቡድን ለመውጋት መሆኑ ይታወሳል፡፡ በአጠቃላይ ሀገሪቱ ወደ ኢራቅ የላከችው ሃይል ወደ 900 ይጠጋል፡፡ ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡