ያልተገባ ዉህደት ፈጽማችኋል በሚል የተከሰሱት አምቦ ዉሃ እና ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ዉድቅ ተደረገባቸዉ፡፡

ያልተገባ ዉህደት ፈጽማችኋል በሚል የተከሰሱት አምቦ ዉሃ እና ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ዉድቅ ተደረገባቸዉ፡፡
አምቦ የማዕድን ዉሃ አክሲዮን ማህበር እና ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አክሲዮን ማህበር በኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር ዉህደት እና የዉህደት ቅንብር ፈጽመዋል በሚል በፌደራል ሸማቾች እና የንግድ ዉድድር ባለስልጣን በቀረበባቸዉ ክስ መሰረት ሰኔ 26 ቀን 2009 አ. ም ላይ በዋለዉ ችሎት የ አንደኛ ተከሳሽ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ጠበቃ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ ችሎቱ ዛሬ ነሃሴ 17 2009 አ.ም ብይን ሰጥቷል፡፡
ጠበቃዉ በመቃወሚያቸዉ ዉህደት ወይም ቅንብር መኖርን የሚመለከት የክስ ምክንያት ስለሌለ ክሱ ዉድቅ እንዲደረግ ለ ችሎቱ ጠይቀዉ የነበረ ሲሆን የባለስልጣን መ/ቤቱ የክስ ባለሞያ በበኩላቸዉ ጉዳዩ የህዝብ እና የመንግስት ነዉ ይህ ህጋዊ ያልሆነ ዉህደት በመፈጸሙም እንደ ሀገር ብዙ የሚታጣ ነገር አለ ሲሉ መቃወሚያዉ ዉድቅ እንዲሆን ጠይቀዉ ነበር ፡፡
በዛሬዉ እለት በዋለዉ ችሎትም ባለስልጣን መ/ቤቱ በአዋጁ በተቀመጠዉ መሰረት የመክሰስ መብት ስላለዉ እና የተጠቀሱት ምክንያቶች አሳማኝ ሆነዉ በመገኘታቸዉ ችሎቱ የ አንደኛ ተከሳሽን መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል፡፡
በዚህም በሁለቱም በከሳሽ እና ተከሳሽ በኩል የቀረቡት ማለትም
በህጉ ዉህደት እና የዉህደት ቅንብር በአዋጁ መሰረት አንድ ናቸዉ ወይስ የተለያዩ ናቸዉ በሚል፤
ተከሳሾች ህጉ ከሚያዘዉ ዉጪ የዉህደት ስምምነት ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም በሚል እና
ዉህደት ተፈጽሟል ከተባለስ የሚጠየቀዉ ዳኝነት ምንድነዉ በሚሉት 3 ጭብጦች ላይ የቃል ክርክር ለማድረግ ችሎቱ ለ ጳሉሜ 1 ቀን 2009 አ.ም ቀጠሮ ይዟል፡፡
ዘገባዉ የእጹብድንቅ ሀይሉ

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.