አገር አቀፍ ዜናዎች

ግንቦት 15/2008 ዓ.ም

ድርጅቱ በኢትዮጵያ ቢሮውን መክፈቱን አስመልክቶ ዛሬ ባካሄደው ጉባኤ ላይ የዓለም የሜትሪዎሎጂ ድርጅት (WMO) ዋና ፀሐፊ ፕሮፌሰር ፒተሪ ታላስ ተገኝተዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ የዓለም የሜትሪዎሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ቢሮውን ወደ አዲስ አበባ ሲያዛውር ስራውን በቅርበት እና በተሻለ መልኩ ለማከናወን እንዲረዳው በማሰብ ነው ብለዋል፡፡  

የኢፌዴሪ ውሃ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ በበኩላቸው የዓለም የሜትሪዎሎጂ ድርጅት ቢሮውን ከስዊዘርላንድ ጄኔቫ ወደ አዲስ አበባ በማዘዋወሩ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለቢሮው እንቅስቃሴ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ዛሬ ጥቁር አንበሳ አካባቢ በሚገኘው የብሔራዊ ሜትሪዎሎጂ ኤጀንሲ ግቢ የአፍሪካ ቢሮውን በይፋ ከፍቷል፡፡ (እንደገና ደሳለኝ)

ግንቦት 09/2008 ዓ.ም

ቤተ-ክርስቲያኗ በልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ኮምሽን በኩል ባበረከተችው ድጋፍ በኤሊኖ ምክንያት የድርቅ አደጋ በደረሰባቸው የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ከ 238,000 በላይ ዜጎችን መርዳት ችያለሁ ብላለች፡፡ ቤተ-ክርስቲያኗ ባዘጋጀቻቸው 230 ያህል ፕሮጀክቶች በዋናነት በትግራይ በአማራ ኦሮሚያ በደቡብና ሶማሊያ የሚገኙ ዜጎችን ረድታለች፡፡ የእርዳታ መርሃ ግብሩም የዘር አቅርቦት አልሚ ምግብ ማከፋፈል የፍየል እና ጊደር ልገሳ እንዲሁም የእርሻ መሳሪያዎችን መለገስን ያካተተ ነው ይላሉ የቤተክርስቲያኗ የልማትና የማህበራዊ አገልግሎት ኮምሽን ኮምሽነሩ አቶ ግርማ ቦሪሼ፡፡ (እንየው ቢሆነኝ)

ግንቦት 09/2008 ዓ.ም

ታላቁ የኢትዮጵያውያን እና አፍሪካውን የነፃነት ተምሳሌት በሆነው በአድዋ ድል ስያሜ የተሠጠው “አድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ” የተሰኘውን ግዙፍ የትምህርት እና የምርምር ተቋም በኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የምስረታ ቻርተሩ ቀርቦ በምሁራን ምክክር ተደርጎበታል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምስረታ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ቢተው በላይ እንደተናገሩት የአድዋ ድል የድል ታሪክ ከመባል ባለፈ በወቅቱ ምን እንደተሰራ፣ ምን እንደተፈፀመ እና ድሉ እንዴት ሊገኝ እንደቻለ፤ ብሎም ከድሉ ጀርባ እነማን እንደነበሩ ጭምር በስፋት ሊቃኝበት የሚችል የታሪካችን ማዕከል እንዲሁም የጥናትና ምርምር መከወኛ ቦታ እንዲሆን እቅድ ተይዞለታል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከአፍሪካና ከመላው አለም ሀገራት የሚመጡ ምሁራን ስለ አድዋ የሚፈልጉትን አይነት መረጃ በቀላሉ የሚያገኙበት የምርምር ስራቸውንም የሚከውኑበት እንዲሆን ለማስቻል ታስቧል፡፡

ዶ/ር አየለ በክሪ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው መመስረት ዋነኛ አላማ የድሉን ታላቅነት ለትውልድ ከማስተላለፍ ባለፈ የ2063 የአፍሪካ የልማት አጀንዳን እውን ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡ በአፍሪካ ታሪካዊና ባህላዊ ሁነት ላይም ትኩረቱን ያደርጋል፣ ሀገራችንም የአህጉሪቱ የታሪክ ዳራ ትሆናለች የሚል እምነትን ይዘናል ብለዋል፡፡

በጦርነቱ ወቅት እና በልዩ ልዩ ጊዜያት ከሀገር የወጡ ቅርሶችን በማስመለስ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራቸው እና ለጎብኚዎችም ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ጋርም በጋራ እንደሚሰራ ተነግሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲውን የማቋቋም እንቅስቃሴው አምና የተጀመረ ሲሆን የመመስረቻ ፅሁፍ ከማዘጋጀት አንስቶ የጋራ ውይይት በማድረግና ምሁራንንም በማሳተፍ ዘልቆ መሻሻል አለባቸው የተባሉ ጉዳዮች ላይም የሀሳብ ግብዓትን ሰብስቧል፡፡ ባለ ሶስት ነጥብ የአቋሙን ይፋ ያደረገው ኮሚቴው 25 አባላትንም መርጧል፤ ነሐሴ ላይም አለም አቀፍ ጉባኤ ለማከናወን ቀጠሮ ይዟል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ግንቦት 08/2008 ዓ.ም

አያሌ አትሌቶችን ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ያበረከቱት ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ በሰሜን ሸዋ ተጉለት እና ቡልጋ ጥር 1939 ዓ ም የተወለዱ ሲሆን ፤ በትምህርቱ አለምም ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደ ምስራቅ አውሮፓ ሀንጋሪ በማቅናት በባዮሎጂ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪ ሰርተው ተመልሰዋል፡፡

የአትሌቲክስ አሰልጣኝነትን የጀመሩት በኮተቤ ኮሌጅ አስተማሪ እያሉ በ70ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሲሆን በ1972 የሙኒክ ኦሎምፒክ በሚሳተፈው ቡድን ውስጥ ዋና አሰልጣኝ ለነበሩት ንጉሴ ሮባ ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ነበር፡፡

ዶክተር ወልደመስቀል በ1982 የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከተቀበሉ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በስፖርት ኮሚሽን ውስጥ በከፍተኛ ባለሙያነት አገልግለዋል፡፡

1992 ዓ.ም የአትሌቲክስ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ የነበሩትን ንጉሴ ሮባን ኅልፈተ ህይወት ተከትሎ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት የያዙት ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ ዛሬም ድረስ በአለም የአትሌቲክስ ታሪክ ስማቸው ከፍ ብሎ የሚጠራ አያሌ አትሌቶችን ለሀገር ማበርከት ችለዋል፡፡
በዚህ የአሰልጣኝነት ጊዜያቸውም ከባርሴሎና ኦሎምፒክ እስከ ቤጂንግ የ2008 ኦሎምፒክ  ውድድር ድረስ ለ16 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ የ5000 እና የ10,000 ሜትር አትሌቶችንም ማብቃት ተችሎዋቸዋል፡፡

ዶ/ር ወልደመስቀል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንን እያሰለጠኑ በተሳተፉባቸው አምስት ኦሎምፒኮች ላይ 13 የወርቅ፣ 5 የብር እና 10 የነሐስ፤ በጥቅሉ 28 ሜዳሊያዎችን ለሀገራቸው አስገኝተዋል ፡፡

እ.ኤ.አ በ2006 ከዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአትሌቲክሱ ዓለም ለአሰልጣኞች የሚሸለመውን የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝነት ሽልማትን ተቀብለዋል፡፡ ዶ/ር ወልደመስቀል በስፖርት ዘርፍ የ2007ዓ.ም የበጎ ሠው ሽልማትንም ተቀብለዋል።

አምና የጭንቅላት ቀዶ ጥገና ህክምና አድረገው የነበረ ሲሆን ከዛ ጊዜ ጀምሮ በአልጋ ውለዋል፡፡ ግንቦት 7 ቀን 2008 ዓ.ም በ69 ዓመታቸው ህይወታቸው አልፏል፡፡ የቀብ ስነ-ስርዓታቸውም በነገው ዕለት ከቀኑ 9፡00 ሰዓት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ-ክርስቲያን ይፈፀማል፡፡

ግንቦት 05/2008 ዓ.ም

መቀመጫውን ኒውዚላንድ ያደረገውና ላለፉት 130 አመታት በአለም ገበያ ላይ ሲሰራ የቆየው አንከር ወተት ወደ ሀገራችን ገብቶ ጥናትና ዝግጅት ካጠናቀቀ በኋላ ምርቱን ማቅረብ ከጀመረ ዘጠኝ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ድርጅቱ ከገበያ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ያለውን የአመጋገብ ስርአት ለማሻሻል የሚረዱ ጥናቶችን በመላ ሀገሪቱ አጠናቆ ለውጥ ለማምጣት እየሰራ እንደሚገኝም በኒውዚላንድ ወተት የኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ አቶ ዚኮ ቃሲም ገልጸዋል፡፡ ስለሆነም በትምህርት ቤቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን ያካሂዳል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ የአንከርን ወተት የሚገዙ ደንበኞቹ በሚደርሳቸው ኩፖን ላይ በእጣ የተለያዩ ሽልማቶችን አዘጋጅቷል፡፡ ሽልማቶቹ ለ100 ሰዎች ባለ 10 ሺህ ብር የተማሪዎች የቁጠባ ሂሳብ ያላቸው የባንክ ደብተሮች፤ 500 የህፃናት ሳይክሎች፤ 500 የተማሪ ቦርሳዎች፣ 1,000 የምሳ እቃዎች፣ 500 ኳሶችን እና 12,000 የአንክር ወተት መጠጫ ኩባያዎችን ያጠቃልላል፡፡ በጥቅሉ 26,000 ስጦታዎችን አዘጋጅቷል፡፡ ደንበኞች በኩፖናቸው ላይ ፍቀው የሚያገኙትን ማንኛውም ሽልማት በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሄድ ሽልማታቸውን መቀበል ይችላሉም ተብሏል፡፡ 

(እንደገና ደሳለኝ)

ግንቦት 04/2008 ዓ.ም

በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ቡድኑ ኢትዮጵያውያንን ገድያለው ስለማለቱ ተጨማሪ መረጃ የለንም ሲል የመንግስት ኮሚዬኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ መንግስት አልባ በሆኑ ሀገራትና ቡድኑ በሚንቀሳቀስባቸው አከባቢዎች ጉዞ ማድረግ ለዚህ አይነቱ ጉዳት ያጋልጣል ያሉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዬች ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ ላይ አይ.ኤስ በኢትዮጵያውያን ላይ በትክክል ድርጊቱን ባይፈጽም እንኳን ቡድኑ ይህን ይፋ ማድረጉ ብቻ የኢትዮጵያውያንን ልብ የሚሰብር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተለይም ከትናንት ምሽት ጀምሮ የኢራን ቴሌቪዢን 16 ኢትዮጵያውያን በአይ.ኤስ መገደላቸውን ሲዘግብ አምሽቷል፡፡ (ነጋሽ በዳዳ)

ግንቦት 04/2008 ዓ.ም

ለጋዜጣው መዘጋት መንግስት በመገናኛ ብዙሀን ላይ የሚከተለው አሰራር አንዱ ምክንያት መሆኑን የሳምሶን አድቨርታይዚንግ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ሳምሶን ማሞ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡ ጋዜጣውን ለመደጎም ድርጅቱ በየወሩ እስከ 100 ሺህ ብር በማውጣት ባለፉት አመታት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጭ ማድረጉንና ይህም ለኪሳራ ዳርጎናል ያሉት አቶ ሳምሶን ከዚህ በላይ መቀጠል ባለመቻላችን ጋዜጣውን ለመዝጋት ተገደናል ብለዋል፡፡ ኢትዮ-ቻናል ጋዜጣ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ 20 ያህል ሰራተኞች የነበሩትና በማህበራዊ ጉዳይ በኪነ-ጥበባት በስፖርትና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ሲሰራ የቆየ ጋዜጣ ነው፡፡ ወደፊት በምን አግባብ እንደምንቀጥል አልወሰንም ያሉት አቶ ሳምሶን ወደ መፅሄት የመዞር እቅድም እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ (እንደገና ደሳለኝ)

ሚያዚያ 28/2008 ዓ.ም

ትናንት ምሽት 12 ሰዓት ገደማ ቦሌ አካባቢ በግንባታ ላይ በሚገኘው አዲሱ ብሔራዊ ስታዲየም ፕሮጀክት የቁፋሮ ስራ ይሰሩ በነበሩ ሰራተኞች ላይ አፈር ተደርምሶ ሁለት ወጣቶች ህይወታቸው ሲያልፍ ሌሎች 11 ሰራተኞች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በአደጋው ህይወታቸው ያለፈው የ25 እና የ27 አመት ወንዶች ናቸው፡፡ ሰራተኞቹ በስራ ቦታቸው ላይ ምንም አይነት የደህንት አልባሳትን አለማድረጋቸውንም መረጃውን የነገሩን የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ገልፀውልናል፡፡

ሚያዚያ 25/2008 ዓ.ም

እሁድ እለት በተከበረው የትንሳኤ በዓል ዋዜማ በተለያዩ ቦታዎች የሞትና የከባድ ጉዳት አደጋዎች ተመዝግበዋል፡፡ በእለተ ቅዳሜ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሃይሌ ጋርመንት አካባቢ ሶስት ወጣቶች በኤሌክትሪክ አደጋ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በዚሁ ክ/ከተማ ሃና ማርያም በሚባለው አካባቢ በእያቄም ትምህርት ቤት የእሳት አደጋ ደርሶ 10,000 ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡ ለገጣፎ አካባቢም በጎርፍ አደጋ የአንዲት ሴት ህይወት አልፏል፡፡

የበዓሉ እለት ደግሞ 43 የትራፊክ አደጋዎች ተመዝግበዋል፡፡ ሁለቱ የሞት እና ሁለቱ ከባድ ጉዳት መሆናቸውን ሰምተናል፡፡ ከተመዘገቡት የሞት አደጋዎች መካከል አንዱ በየካ ክፍለ ከተማ ላምበረት መናኸሪያ አካባቢ የደረሰ ሲሆን ተጎጂው በኮሪያ ሆስፒታል ህክምና ሲደረግለት አምሽቶ ሌሊት ሰባት ሰአት ህይወቱ አልፏል፡፡ ሌላኛው የሞት አደጋ ደግሞ በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አካባቢ የደረሰ ሲሆን ተጎጅው ወዲያው ህይወቱን አጥቷል፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማም እንዲሁ በከሰል ጭስ ምክንያት የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን ሰምተናል፡፡ መረጃውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው ም/ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ እና ከአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ንጋቱ ማሞ አግኝተነዋል፡፡

ሚያዚያ 21/2008 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ሰራተኞችን በማህበር የማደራጀት እና የመደገፍ አላማ ያለው ሲሆን መብታችውን እና ጥቅማቸውን ለማስከበር እንዲችሉ በማደራጀቱ በኩል የላቀ ሚና ይጫወታል፡፡ ሰራተኞች በማህበር ካልተደራጁ ለሚፈጠሩ ችግሮች ብሎም የመብት ጥያቄን በተገቢው መንገድ ለማስከበርም ይሁን ለመጠየቅ እንደማይችል ኮንፌደሬሽኑ አስታዉቋል፡፡ ሰራተኞች የመደራጀት መብት እንዳላቸው ግንዛቤ የመፍጠር እና ሰራተኞችም በምን አይነት መልኩ ተደራጅተው መብታቸውን ማስከበር እንዳለባቸው ማሳወቅ ሌላኛው የአሰሪዎች ተግባር መሆኑን የኢትዮጲያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ካሳሁን ፎሌ ተናግረዋል፡፡ በማህበር ላልተደራጁ ሰራተኞች ምንም አይነት እርዳታ ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነና በማህበር ቢታቀፉ ዘርፈ ብዙ የሆነ ጠቀሜታ እንደሚያገኙም ተገልጧል፡፡ የመንግስት ሰራተኞችም በማህበር የመደራጀት መብት እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን ለኮንፌዴሬሽኑም መጠናከር የሚኖረው ጠቀሜታ ላቅ ያለ መሆኑን የኢትዮጲያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ካሳሁን ፎሌ ተናግረዋል፡፡ (ርብቃ ታያቸው)

ሚያዚያ 20/2008 ዓ.ም

ኤጀንሲው የ2008 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የብሔራዊ ፈተና መውሰጃ የጊዜ ሰሌዳን ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ 10ኛ ክፍል ፈተና ከግንቦት 17-19/2008 ዓ.ም ይሰጣል። በተመሳሳይም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከግንቦት 22-25/2008 ዓ.ም እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡

ሚያዚያ 17/2008 ዓ.ም

1998 ዓ.ም ላይ ከባድ የጎርፍ አደጋን አስተናግዳ የነበረችው የድሬዳዋ ከተማ ከ10 አመታት በኋላ ዳግም ይህን መሰል አደጋ ማስተናገዷ ነው የተሰማው፡፡

ሚያዚያ 17 ማለዳ 12፡30 ላይ የተከሰተው ይህ የጎርፍ አደጋ 4 ሰዎችን በጎርፉ እንዲወሰዱ ያደረገ ሲሆን “የ23 ዓመት ወጣት የሆነው ግለሰብ ከቀፊራ ማረሚያ ቤት እስከሚባለው አካባቢ በጎርፏ ከተወሰደ በኋላ ማረሚያ ቤት የሚባለው አካባቢ ላይ ሲደርስ ጎርፉ ተፋው፤ ህይወቱም በተዓምር ተረፈች፤ 3 ያህሉ ሰዎች ግን ህይወታቸው አለፈ” ሲሉ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ሃላፊው ዋና ኢንስፔክተር ገመቹ ካቻ ለዛሚ ተናግረዋል፡፡

በጎርፉ ከድሬዳዋ ወደ መልካ ጀብዱ የሚወስደው ድልድይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፣ ከ12 በላይ በጎችና 2 ዩዲ ትራክ መኪኖችም በጎርፉ ተወስደዋል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም በድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር ገመቹ ካቻ ነግረውናል፡፡

ሚያዚያ 17/2008 ዓ.ም

የፋሺስት ኢጣልያ ወራሪ ሰራዊት ድል የተመታበትን 75ተኛ አመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በአሉን ለማክበር ዝግጅቱን ያጠናቀቀው የጀግኖች አርበኞች ማህበር በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ አርበኞችን በማሰባሰብና በያሉበትም በመድረስ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፏን እያደረገ ይገኛል፡፡

የወቅቱ ድል እንዲገኝ አብይ ምክንያት የሆኑት አርበኞች ገሚሶቹ ህይወታቸው ሲያልፍ የተቀሩት ደግሞ በህይወት ይገኛሉ፤ በህይወት የሚገኙት አርበኞች ቁጥር ግን በማበሩ በውል እንደማይታወቅ ነው ከማህበሩ ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የሰማነው፤
በማህበሩ ሰንድ ውስጥ የሚገኘው በህይወት ያሉ አርበኞች ቁጥር ከ42-45 ሺህ ይገመታል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህ ግን ግምታዊ ቁጥር ነው እንጂ እርግጠኛ ቁጥር አይደለምም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ትክክለኛውን በህይወት ያሉ አርበኞችን ቁጥር ለማወቅ አሁን ላይ በየዞኑና በየወረዳው አርበኞችን ፍለጋና ምዝገባ እየተደረገ ነው ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ሚያዚያ 14/2008 

 

በመዲናችን አዲስ አባባ በየወሩ 4.6 ሚሊየን ሊትር ዘይት ለገበያ ይቀርባል፤ ሰኳር ደግሞ በየወሩ 108,000 ኩንታል፡፡ ይሄን አቅርቦት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለማዳረስና በአሉን አስመልክቶ ምንም እጥረትም ሆነ የዋጋ መናር እንዳይኖር እየሰራሁ ነው ይላል የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ፡፡ በከተማዋ በሚገኙ 575 የማህበራት ሱቆች እና ከ50 ሺ በሚልቁት የሸቀጣሸቀጥ ሱቆች ምርቶቹ በበቂ ሁኔታ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ በዋነኛነት እጥረቱ የሚከሰተው በዱቄት አቅርቦት ላይ ሊሆንም ይችላል የሚሉት የንግድ ቢሮው ሃላፊ አቶ ርስቱ ይርዳ በመዲናችን በወር ለዱቄት የሚቀርበው የስንዴ መጠን 120 ሺ ኩንታል ሲሆን ይሄም ወደ ዱቄት ሲቀየር ከ80 ሺ አይበልጥም ይላሉ፡፡ መንግስትም ከዚህ በላይ ማቅረብ እንዳልቻለ ሰምተናል፡፡ ለበአል ለእርድ የሚቀርብ ሰንጋ እጥረት እንዳይኖርም ንግድ ቢሮው ከኦሮሚያ ህብረት ስራ ማህበራት ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር በሞጆ ከተማ በተዘጋጀ የገበያ ቦታ የቦረና የእርድ በሬዎች ለገበያ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ በባህላዊ እርድ ስርአት በየቤቱና በየመንደሩ ለቅርጫ የሚታረዱ በሬዎች ማህበረሰቡ ጤንነታቸው የተጠበቀ መሆናቸውን በማረጋገጥ ሊጠቀም እንደሚገባም ሃላፊው ተናገረዋል፤ በህገ-ወጥ እርድ ጤናማነቱ ያልተረጋገጠ 6424 ኪሎ ግራም ስጋ ተይዞ መቃጠሉንም በማስታወስ፡፡ ለበዓሉ የአትክልትና ፍራፍሬ እጥረት እንዳይኖርም የሸማቾች ማህበራት ሙሉ ዝግጅት አድርገዋል ተብሏል፡፡ (እንየው ቢሆነኝ)

ሚያዚያ 13/2008 ዓ.ም

ዩኒሴፍ በቃል አቀባዩ በኩል በላከው መግለጫ ከ100 በላይ ህፃናት መታገታቸውን እና ከተገደሉትም መካከል ህጻናት መኖራቸው ድርጊቱን የከፋ ያደርገዋል ብሏል፡፡ ቃል አቀባዩ አያይዘውም ዩኒሴፍ ተጎጂ ህጻናቱን ለመርዳትና ታፍነው የተወሰዱትም እንዲመለሱ ከማህበረሰቡ ጎን ይቆማል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ህጻናቱን ለማስመለስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በማፋጠን በቶሎ ወደቤታቸው እንዲመለሱ ዩኒሴፍ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

(ሽንዋ)

ሚያዚያ 11/2008 ዓ.ም

በጋምቤላ ብሄራዊ ክልል የደቡብ ሱዳን ወገን እንደሆነ የሚነገርለት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂ ሀይል በፈፀመው ጥቃት እስካሁን 208 ንፁሀን ዜጎች የተገደሉ ሲሆን 102 የሚያህሉ ሴቶችና ህጻናት በታጣቂ ሀይሉ ታፍነው ተወስደዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ድርጊቱ ኢ-ሰብአዊ ተግባር በመሆኑ በሁሉም ሀይማኖቶች የተወገዘ ነው ብሏል፡፡

ጉባኤው በታጣቂ ሃይሉ ታፍነው የተወሰዱ ወገኖች እንዲመለሱ ለማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ የማድረግ ቁርጠኝነት እንዳለው ገልጧል፡፡ በተጨማሪም ሁኔታው ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይደርስ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደየእምነታቸው በፀሎት እንዲተጉ አሳስቧል፡፡

በሌላ በኩል ከግብፅ ወደ ጣሊያን በህገ-ወጥ መንገድ ለመግባት በአነስተኛ ጀልባ ላይ ሲጓዙ የነበሩ ተጓዦች ጀልባዋ በመስጠሟ ህይወታቸው አልፏል፡፡ አብዛኞቹም ኢትዮጵያውያን፣ የሶማሊያ እና የኤርትራ ዜጎች ናቸው፡፡

ጉባኤውም በአደጋው ተጎጂ ለሆኑ ቤተሰቦች መፅናናትን የተመኘ ሲሆን ህገ-ወጥ የሠዎች ዝውውርንም በጋራ እንከላከል የሚል ጥሪ አስተላልፏል፡፡

ምንጭ - የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

ሚያዚያ 11/2008 ዓ.ም

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ድረ-ገጽ እንዳስነበበው ሊቀመንበሯ ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ በጋምቤላ ክልል ጃካዋ አካባቢ የተፈጸመውን ጥቃት አጥብቀው ያወገዙ ሲሆን ኮሚሽኑ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጎን እንደሚቆምም አመልክተዋል።

ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ የተጠለፉ ህጻናትና ሴቶች እንዲለቀቁ ጽኑ ጥረት እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡ አያይዘውም የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን መንግስታት በጋራ በመሆን ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ እንደሚኖርባቸውና ሕብረቱም ከዚህ ጥረት ጎን እንደሚሰለፍ ተናግረዋል።

ሚያዚያ 11/2008 ዓ.ም

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጋምቤላ ክልል በታጣቂዎች ህይወታቸው ያለፈ ንፁሃን ዜጎችን ለማሰብ ከነገ ረቡዕ ጀምሮ የሁለት ቀናት ብሄራዊ የሀዘን ቀን አውጇል፡፡

ምክር ቤቱ ከነገ ጀምሮ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በውጭ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ፅ/ቤቶች ለሁለት ቀናት የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ወስኗል።

በተመሳሳይ ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ የሆኑ መርከቦችም ከነገ ጀምሮ የኢፌዴሪ ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ የሚያደርጉ ይሆናል።

ባሳለፍነው አርብ ምሽት በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች በደቡብ ሱዳን በኩል ድንበር ሰብሮ በመግባት በንጹሃን ዜጎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት ቁጥራቸው ከ208 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

እንዲሁም ቁጥራቸው 108 የሚደርስ ህጻናት በታጠቁት ሀይሎች ታፍነው ተወስደዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትም ጥቃት ፈጻሚ ወንበዴዎችን ድንበር በመሻገር እርምጃ እየወሰደባቸው ሲሆን፥ ከ60 የሚበልጡ ጥቃት ፈጻሚዎች ተገድለው የጦር መሳሪያም ተይዟል።

በአሁኑ ጊዜም በታጣቂዎች ታፍነው የተያዙትን የማስለቀቁ ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ምንጭ - የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት