አገር አቀፍ ዜናዎች

ህዳር 16/2008 ዓ.ም

ናይል ማራቶን የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ የመሮጫ ስፍራ በሀገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ለሚደረግ የማራቶን ሩጫ ውድድር እንዲያገለግል ታስቦ የሚሰራ ሲሆን የዲዛይን ጥናቱን ከባህርዳር ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን አባ የአርክቴክት ስራዎች ድርጅት ማጠናቀቁን የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አዲስ አዱኛ ተናግረዋል፡፡ ናይል ማራቶን ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ወደ ባህርዳር ከተማ የሚመጡ ቱሪስቶችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ማራቶንን ጨምሮ በረጅም ርቀት የሩጫ ውድድር የሚታወቁ አትሌቶች ባለቤት ብትሆንም ለማራቶን የመሮጫ ስፍራ ባለመኖሩ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ የሚያብራሩት ስራ አስኪያጁ አቶ አዲስ ስራው በሚከናወንበት የወንዙ ዳርቻ እና በአጠቃላይ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳትን ለመጎብኘት እድል የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሩጫው የሚጀመርበት የጣና ሃይቅ ዳርቻና የሚጠናቀቅበት የጭስ አባይ ፏፏቴ ልዩ መስህብ ያላቸው ስፍራዎች በመሆናቸው ተሳታፊዎች ውድድሩን የበለጠ እንዲወዱት የሚያደርግ ቦታ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ የባህርዳር ከተማ ከንቲባም በበኩላቸው ይህ ፕሮጀክት ለከተማዋ የበለጠ ድምቀት የሚሰጥ እና በቱሪዝም ዘርፍ ገቢ ለማግኘት የሚረዳ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ለማከናወን በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ልዩ ልዩ ዘመናዊ ድልድዮችም የግንባታው አካል እንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡ 

ህዳር 15/2008 ዓ.ም

ሀገራችን ከዓለም የቱሪዝም መዳረሻነት ቀዳሚ በሆነችበት በዚህ ዓመት የቱሪዝሙን እንቅፋቶች በማስንሳት ኢንዱስትሪውን ማሳደግ አለብን ተብሏል፡፡

በዋና ዋና የቱሪዝም መዳረሻዎች የተሟላ መሰረተ ልማት አለመኖር፣ የመግባቢያ ቋንቋዎች ክፍተት፣ የተሟላ መረጃ ለጎብኚዎች አለመስጠት እና ሌሎችም በዘርፉ እድገት ላይ የተደቀኑ ችግሮች ናቸው ተብሏል፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ወይንሸት ሃ/ማርያም በዋና ዋና የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ ህፃናት ለወሲብ ንግድ እንዳይጋለጡ መከላከል ዋነኛ ተቀዳሚ ስራችን ነው ብለዋል፡፡ (እንየው ቢሆነኝ)

ህዳር 15/2008 ዓ.ም

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ተከትሎ አሰራሮችን በመፈተሽ የህዝቡን የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በሚያስችል መልኩ መራመድ ባልቻለው የመረጃ ነፃነት ችግር ላይ ውይይት እየተደረገ ነው፡፡

ውይይቱ በሀገር ደረጃ የተሻለ አፈፃፀም እንዲመጣ ህብረተሰቡ መረጃ የማግኘት መብቱ እንዲከበርለት የመንግሥት አሰራር ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግ በኩል ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ውይይቱን ያዘጋጀው የኢፌዴሪ እንባ ጠባቂ ተቋም ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ሲሆን የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊዎች የውይይቱ ተሳታፊ ናቸው፡፡

ህዳር 14/2008 ዓ.ም

በኦሮምያ ክልል አርሲ ዞን በድሬ ቂልጦ ቀበሌ በድርቅ ምክንያት ነዋረዎች ችግር ውሰጥ ናቸው ተብሏል። ሁለት ግዜ የምግብ ድጋፍ ቢደረግላቸውም በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል። እንሰሳቶቻቸው በመኖ እና በውሃ እጦት ችግር ውስጥ ናቸው። የወረዳው የአደጋ መከላከል ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ጣሂር ፊኒኖ የምግብ ድጋፍ እየደረጉ መሆናቸውን በመግለፅ የውሃ እና የእንሰሳት መኖ ጥያቄ ቢያቀርቡም የክልሉ መሰተዳደር ምላሽ እንዳልሰጣቸው ተናግረዋል። ከ84 ሺህ 396 ነዋሪዎች ውስጥ 51 ሺህ 936 የሚሆኑት እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከሰኔ እሰከ ጥር 2008 ድረስም 5 ሺህ 297 አዲስ ተጉጂዋች እንደሚጠበቁ ተገምቷል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

ህዳር 13/2008 ዓ.ም

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የተጎጂዎችን ቁጥር በመጨመር የሚደረገውን እርዳታ ለግል ጥቅማቸው ሲያውሉ ከህብረተሰቡ በተደረገ ጥቆማ መሰረት መረጃዎች በመገኘታቸው መሆኑ ታውቋል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

ህዳር 13/2008 ዓ.ም

በዞኑ ከሚገኙ 19 ወረዳዎች 8ቱ በድርቅ ተጎድተዋል፡፡ በሚዳ ቶላ እና ኩሩፋ ጨሌ ወረዳዎች ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው ድርቁ ያስከተለባቸው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ማሳቸው በመጎዳቱ ምክንያት ምርቶቻቸው ለከብቶቻቸው ቀለብ ሆነዋል፡፡

ተጎጂዎቹ በመንግስት እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ የዞኑ ከፍተኛ ገቢ የጫት ምርት ሲሆን ይህም ከገቢው 70 በመቶ ያህል ድርሻ አለው፡፡

በዞኑ ይሰበሰባል ተብሎ የታሰበው 13 ሚሊዮን ኩንታል እህል ሲሆን በደርቁ ምክንያት ወደ 3 ሚሊየን እንደሚያዥቆለቁል የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደምሴ ያቼሴ ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው ከፍተኛ የውሃ እጥረት በማጋጠሙ 17 የቦቴ ተሸከርካሪዎች በየቀኑ ለህብረተሰቡ ውሃ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን ከህዝቡ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ በመሆኑ ተጨማሪ ቦቴዎች እንደሚያስፈልጉ የዞኑ አስተዳዳሪ አስታውቀዋል፡፡

የጤና ሁኔታን በተመለከተ ክትትል እየተደረገና ለህጻናትም አልሚ ምግቦች እየተሰራጩ ነው ተብሏል፡፡

በድርቁ እስካሁን በዞኑ በሰው ላይ የደረሰ የሞት አደጋ ባይኖርም ድርቁ ከመከሰቱ ጋር ተያይዞ እንስሳት መሞታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

ህዳር 11/2008 ዓ.ም

ከዛሬ ህዳር 11 እስከ ህዳር 25 ቀን 2008 ዓ.ም የሴካፋ ውድድር፣ እንዲሁም ነገ ህዳር 12 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄዱ መሆናቸውን ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሚያካሂደውን የፀጥታ ጥበቃ ስራ ለማገዝ ለአጭርና ለረጅም ጊዜ ዝግ የሚሆኑና ተሸከርካሪን ለማቆም የተከለከሉ መንገዶችን ገልጧል፡፡

በዚህም መሰረት 38ኛው የሴካፋ ውድድር በሚካሄድበት ብሄራዊ ስታዲየም አካባቢ ዛሬና ነገ የመክፈቻ ውድድሮች ሲካሄዱና ከህዳር 19 ጀምሮ እስከ ህዳር 25 ድረስ ባሉት ቀናት፡-

 • ከሳንጆሴፍ መብራት እስከ ለገሃር መብራት
 • ከአረንጓዴ ጎርፍ ሆቴል እስከ ክቡ ባንክ
 • ከክቡ ባንክ እስከ ቀይ መስቀል እና
 • ከሃራምቤ እስከ ጊዮን ሆቴል ድረስ ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ተሸከርካሪን አቁሞ መሄድ የተከለከለ መሆኑ ተገልጧል፡፡

እንዲሁም 15ኛው ታላቁ ሩጫ በሚካሄድበት በነገው ዕለት መድረሻቸውን መስቀል አደባባይ አድርገው ከዑራኤል ቤተ-ክርስቲያን፣ ከኦሎምፒያ፣ ከብሔራዊ ቤተ-መንግስት እና ከሃራምቤ ሆቴል የሚመጡ መንገዶች፤ እንዲሁም፡-

 • ከብሔራዊ ትያትር ወደ ለገሃር
 • ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል ወደ ሜክሲኮ
 • ከብሄራዊ አረቄ ፋብሪካ ወደ ሜክሲኮ
 • ከልደታ ቤተ-ክርስቲያን ወደ ሜክሲኮ
 • ከልደታ ፀበል በአዲሱ መንገድ ወደ አፍሪካ ህብረት አደባባይ
 • ከቡልጋሪያ ወደ አፍሪካ ህብረት አደባባይ
 • ከካርል አደባባይ ወደ ሳር ቤት
 • ከጎፋ ገብርኤል ወደ ጎፋ መስቀለኛ
 • ከቂርቆስ ወደ ቴሌ እና ጎፋ መስቀለኛ
 • ከወሎ ሰፈር ወደ ጎተራ
 • ከሳሪስ ወደ ጎተራ እና
 • ከመስቀል ፍላወር ወደ አጎና ሲኒማ በሚወስዱ መንገዶች ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ተሸከርካሪን ለረጅምም ሆነ ለአጭር ጊዜ አቁሞ መንቀሳቀስ የተከለከለና ለሩጫው መነሻና መድረሻ ከሆነው ከመስቀል አደባባይ ውጪ የተጠቀሱት መንገዶች በትራፊክ ፖሊሶች ትዕዛዝ ሲዘጉ አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም እንዲንቀሳቀሱ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡

በዚህ አጋጣሚም ለማንኛውም ጥቆማና ፖሊሳዊ አገልግሎት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የመረጃ ስልክ ቁጥሮች በ 991 ነፃ ጥሪ፣ በቀጥታ መስመር 0111 11 01 11 እና 0111 26 43 59 መጠቀም እንደሚቻል ተገልጧል፡፡

ህዳር 11/2008 ዓ.ም

መንግስት ለተጎጂዎች መጋዘኖችን በማቋቋም እርዳታ እየሰጠ ቢሆንም የስርጭት እንዲሁም የውሃ ከፍተኛ እጥረት መኖሩን የአካባቢው ነዋሪ አቶ መሐመድ ተናግረዋል፡፡

የውሃ እጥረቱን ለመፍታት ባለሃብቶችና ግለሰቦች ውሃ በማምጣት እያሰራጩ ይገኛሉ፤ ለዚህም እስከ አንድ ብር ድረስ ነዋሪዎቹ እንደሚከፍሉ ተነግሯል፡፡

በዝናብ እጥረት ምክንያት የተከሰተው ድርቅ በማሳዎችና በከብቶች ላይ ጉዳት አስከትሏል፡፡

በሀረርጌ የተጀመረውን ጉብኝት እንዲሁም በደቡብ፣ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች ከድርቁ ጋር ተያይዞ መረጃዎችን እየተከታተልን የምናቀርብላችሁ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

ህዳር 08/2008 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአብራሪ እስከ አስተናጋጅ በሴቶች ብቻ የሚመራ የመጀመሪያ በረራውን በዛሬው ዕለት ሊያደርግ ነው፡፡ በረራው ከአዲስ አበባ ባንኮክ የሚደረግ ሲሆን የአውሮፕላኑ አብራሪ /ፓይለት/፣ የበረራ አስተናጋጅ እና መላው የአውሮፕላን ሰራተኞች ሙሉ በሙሉ ሴቶች እንደሆኑ ተገልጿል። የመጀመሪያ የሆነውና ልዩ የተባለው ይህ በረራ በነገው ዕለት ከአዲስ አበባ በመነሳት ታይላንድ ባንኮክ ደርሶ መልስን ያካተተ ነው።

ህዳር 06/2008 ዓ.ም

በዛሬው እለት ከቀኑ 9፡20 ላይ በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ስፍራው ሽሮ ሜዳ አካባቢ በመዞር ላይ የነበረ 31 ቁጥር አንበሳ የከተማ አውቶብስ የመግጨት አደጋ ካደረሰባቸው ሰዎች መካከል ሶስቱ ለእርዳታ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ህይወታቸው ሲያልፍ ሌላ አንድ ግለሰብ በህክምና ላይ ይገኛል፡፡ በስፍራው የነበሩ ሌሎች ሰዎችም ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡ የአደጋው መንስኤ በመጣራት ላይ ቢሆንም አሽከርካሪው የፍሬን ችግር እንዳጋጠመው ተናግሯል ሲሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ የሆኑት ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ በተለይ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ገልፀዋል፡፡

ህዳር 06/2008 ዓ.ም

ፋብሪካው በጥንታዊቷ ደጋማዋ ከተማ ደብረብርሃን ላይ መቋቋሙ ለከተማይቱ እድገት በተለይም ደግሞ በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ ጎልታ እንድትወጣ ለማድረግ የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ ሌሎችንም ባለሃብቶች ወደ ከተማይቱ ለመጋበዝ እንደምሳሌም ጭምር መሆን ይችላል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃ/ማርያም ደሳለኝ ፋብሪካውን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

ይህ የዳሸን ቢራ ደብረብርሃን ፋብሪካ በሀገራችን ብሎም በአህጉራችን በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የምርት ቴክኖሎጂ የተተከለበት ሲሆን ይህ ቴክኖሎጂ የዘመኑ ምርጥና ቁጥር አንድ የቢራ ጠመቃ ቴክኖሎጂ ነውም ተብሏል፡፡ በአጠቃላይ የግንባታው ወጪ 3 ቢሊዮን ብር ሲሆን በ12 ሄክታር መሬት ላይም አርፏል፡፡ ሁለት ሚሊዩን ሄክቶ ሊትር ቢራም ይጠመቅበታል፤  በሰዓት 180 ሺህ ጠርሙስ ቢራ የማምረት አቅምም አለው፡፡ ከ500 በላይ ለሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠሩም ተነግሯል፡፡

ዳሽን ቢራ በዓመት 4.2 ሚሊዬን ሄክቶ ሊትር ቢራ ያመርታል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ህዳር 02/2008 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የንግድ ኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሪ ዋና የስራ ሂደት የህጋዊ ስነ-ልክ ከፍተኛ ኦፊሰር ለዛሚ እንደተናገሩት ጥቅምት 18 ቀን 2008 ዓ.ም ከአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ዳቦ አምራች ማህበር ጋር በመቀናጀት በተመረጡ ሶስት ክ/ከተሞች ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ላይ በተደረገ የዳቦ ቤቶች የዳቦ ግራም ቁጥጥር ስራ በርከት ያሉ ዳቦ ቤቶች የግራም ማጉደል ተግባርን ሲፈፅሙ ተገኝተዋል፡፡

የስራ ሂደቱ የህጋዊ ስነ-ልክ ከፍተኛ ኦፊሰር የሆኑት አቶ ደረጄ በቀለ እንዳሉት በ33 ዳቦ ቤቶች ላይ በተደረገው የቁጥጥር ስራ ከባለ 100 ግራሙ ዳቦ በአማካኝ 13 ግራም፣ ከባለ 200 ግራም በአማካኝ 37 ግራም እና ከባለ 300 ግራም በአማካኝ 67 ግራም 11 ንግድ ድርጅቶች አጉድለው የተገኙ ሲሆን ከማስጠንቀቂያ ጀምሮም እስከ ማሸግ የደረሰ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል፡፡

በእርምጃው 4 ዳቦ ቤቶች ላይ የቃል ማስጠንቀቂያ፣ ሌሎች 4 ዳቦ ቤቶች የፁሁፍ ማስጠንቀቂያና 3 ዳቦ ቤቶች ላይ የማሸግ እርምጃ ተወስዷል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ጥቅምት 22/2008 ዓ.ም

የአፍሪካ ህብረት የወጣቶች ቀን የአፍሪካ ህብረት የሰው ሃይልና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ከፓን አፍሪካን የወጣቶች ህብረት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው፡፡

የወጣቶች ቀን አከባበር በአፍሪካ ወጣቶች ላይ የግንዛቤ ለውጥ ማምጣቱ ላይ እንዲሁም ወጣቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን የቻሉ እና ለሀገር እድገት የበኩላቸውን የሚወጡ ወጣቶችን ማፍራት ላይ ትረኩቱን አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶች የአፍሪካዊያንን ባህል የሚተዋወቁበት እና የየራሳቸውን ባህል ለሌላ የሚያስተዋውቁበትም ሆኗል፡፡

ወጣቶች በዋናነት በ2063 የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ የወጣት ሴቶች መብት መከበር ላይ ትኩረታቸውን አድርገው ተወያይተዋል፡፡ በዚህ 200 ወጣቶች በተሳተፉበት የአፍሪካ ወጣቶች በዓል አከባበር የ2063  የአፍሪካ ህብረት አጀንዳዎችን ሙሉ በሙሉ ወጣቶች ላይ ያሰርፃል፣ በወጣቶች ላይ የሚሰሩ የተለያዩ ድርጅቶችን ያገናኛል፣ በአህጉሪቱ የሚገኙ ወጣቶችን አቅም ለማዳበር ልምድ ይካፈላሉ፣ በሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ላይ እንዲሁም የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎም ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ትላንትና የተጀመረው የአፍሪካ ወጣቶች በዓል አከባበር ዛሬም ቀጥሎ ውሏል፡፡ (እንየው ቢሆነኝ)

ጥቅምት 22/2008 ዓ.ም

ማህበሩ 9ኛ መደበኛ አመታዊ ጉባዔውን ባደረገበት እለት ነበር ይህን ያሳወቀው፡፡ የኢትዮጵያ እውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማህበር በ1994 ዓ.ም በካሊፎርኒያ የተመሰረተ ሲሆን በ2002 ዓ.ም ነበር በሀገር ውስጥ ሙሉ እውቅና ተሰጥቶት በማህበር ደረጃ መንቀሳቀስ የጀመረው፡፡ ማህበሩ አሁን ላይ በመቐለ፣ በድሬዳዋ እና በሌሎች የክልል ከተሞች ቤተ-መፃህፍት በመገንባት፣ በጤና፣ በግብርና እና በአቅም ግንባታ ዘርፍም ተሰማርቻለሁ ያለ ሲሆን፤ በማረሚያ ቤቶች 13 ያህል ቤተ-መፃህፍት መገንባቱም ተገልጧል፡፡ እነዚህን የማረሚያ ቤቶች ቤተ-መፃህፍት ወደ 20 አሳድጋለሁም ብሏል፡፡ (እንየው ቢሆነኝ)

ጥቅምት 18/2008 ዓ.ም

የዓለም ኢነርጂ ካውንስል ከ30ሺ በላይ የመንግሥት ተቋማትን፣ የግል ድርጅቶችን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑና በሃይል አቅርቦት ዘርፉ ለተሰማሩ ተቋማት በፓሪሱ ጉባዔ የካርበን ልቀት መቀነስን እና ቀጣይነት ያለው የሃይል አቅርቦት ማዳረስ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሀገራት ለዚህ ዓላማ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከጥቅምት 15 ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው በዚህ ጉባዔ ከ86 በመቶ በላይ ህዝብ ምንም የሃይል አቅርቦት አያገኝም በሚባልባት አፍሪካ ፍትሃዊ የሆነ የሃይል ክፍል እንዲኖር እና የአህጉሪቱ መንግሥታት በፀሃይ፣ በነፋስና በውሃ ሃይል በሰፊው እንዲንቀሳቀሱ መክሯል፡፡

የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚ/ር ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ የዓለም ኢነርጂ ካውንስል ይህን ታላቅ ጉባዔ በአዲስ አበባ በማዘጋጀቱ በሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን እቅድ በውሃ፣ በነፋስ እና በፀሃይ ሃይል ዘርፎች ከፍተኛ ስራ ለመስራት ከሚያግዙን አካላት ጋር ተባብሮ ለመስራት ትልቅ መድረክ ሆኗል ብለዋል፡፡

ከተመሰረተ 90 ዓመታትን ያስቆጠረው የዓለም ኢነርጂ ካውንስል ይህ ጉባዔ በአፍሪካ፤ ብሎም በአዲስ አበባ እንዲዘጋጅ ዓለም ትኩረቱን አፍሪካ ላይ እንዲያደርግ በኢንዱስትሪው የበለፀጉ ሀገራት የሚለቁት የካርበን መጠን ከፍተኛ መሆን የአፍሪካን የአየር ፀባይ በእጅጉ እንዲጎዳ ለመሆኑ መልዕክት ለማስተላለፍ መሆኑም ታውቋል፡፡ (እንየው ቢሆነኝ)

ጥቅምት 17/2008 ዓ.ም

በአዲስ አበባ የሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ ከጣሊያን ባህል ማዕከል ጋር በመተባበር ለፋሽን ሳምንቱ ድጋፍ ማድረጋቸው ተዘግቧል፡፡ በጣሊያን ታዋቂ የሆነው የፋሽን ዲዛይነር ማሪና ስፓዳፎራን የተጋበዙ ሲሆን እንዲሁም የጣሊያን የፋሽን ጋዜጠኛ የሆነችውም ሳራ ማሮኖ ተጋባዥ እንግዳ እንደሆኑ የጣሊያን መንግሥት ድጋፍ አድርጓል፡፡

ከዚህም ባሻገር የጣሊያን ኤምባሲ የመጨረሻውን የፋሽን ፕሮግራም ምሽት በኤምባሲው ውስጥ እንዲደረግ በሩን ከፍቷል፡፡ በፕሮግራሙም ላይ ከ300 በላይ ተሳታፊ እንግዶች እና ከ15 በላይ የጨርቃጨርቅ ስፌት ውጤቶች በኤግዚቢሽ መልክ እንደሚጎበኙ ተገልጧል፡፡

የዓለማችን የፋሽን ፍላጎት ወደ ኢትዮጵያና ወደ አፍሪካ ማዘንበሉም የተጠቆመ ሲሆን በዚህ ዘርፍም በጣሊያንና በሌሎች ሀገራት በተለይ ለአፍሪካ ፋሽን ልዩ ትኩረት እንዳላትም ተነግሯል፡፡ ጣሊያንም ወደ ኢትዮጵያ የፋሽን ዘርፍ ለመምጣት ልዩ ፍላጎትና ተሰጥኦ ያላቸውን ሰዎች በማሳደጉ ላይ እንደሚሰራም ተገልጧል፡፡ (ርብቃ ታያቸው)

ጥቅምት 16/2008 ዓ.ም

በጣናና በለስ ንዑስ ተፋሰሶች የአየር ሁኔታ መከታተያ (መረጃ መሰብሰቢያ) ራዳር ተከላ የግዥ ስራው ተከናውኖ ተከላው በ2008 በጀት ዓመት ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ይጠናቀቃል። ተከላው የሚካሄደው በጣና ሃይቅ በስተሰሜን ሻውራ በተባለ ኮረብታማ ቦታ ላይ ነው። የራዳሩ ዋና ክፍልና መሸከሚያው ታወር ተገዝቶ አገር ውስጥ ገብተዋለል፡፡

በአሁኑ ወቅት የራዳር ቤት፣ የጄኔሬተር ቤት፣ ወርክሾፕ፣ ዕንግዳ መረፊያ፣ የጥበቃ ቤት ከ90% በላይ ተጠናቆዋል።

የፕሮጀክቱ ባለቤት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሲሆኑ የራዳር አቅርቦቱን ባይሳላ የተባለ የኔዘር ላንድ አገር ካምፓኒ ሆኖ አማካሪውም ፔጃ የተባለ የኔዘርላንድ አገር ካምፓኒ ነው።

በራዳሩ የሚሰበሰበው የአየር ሁኔታ መረጃ በዋናነት ጠቀሜታው በጣና እና በበለስ ንዑስ ተፋሰሶች ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮች ፣የህብረተሰብ ክፍሎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሲሆኑ ከመረጃው በመነሳት የጎርፍ ሁኔታንም መተንበይ ስለሚቻል ሱዳንና ግብፅም ተጠቃሚ ይሆናሉ።

መሳሪያውን ከሙያ አንፃር የሚጠቀሙ የብ/ሜ/አ/ኤጀንሲ ይሆናል። የራዳሩ ሽፋን ከ 150 ኪሎሜትር እስከ 250 ኪ/ሜትር ይደርሳል። በአጠቃላይ ለራዳር እና ተያያዥ ግዥዎችና ግንባታዎች ከአለም ባንክ በተገኘ 1,540,520ዩሮ (35.5ሚሊዮን ብር) ሲሆን በረዥም ግዜ የሚከፈል ብድር ነው።

ምንጭ - መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር

ጥቅምት 16/2008 ዓ.ም

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ የወንጀል ችሎት በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ አቶ መላኩ ፈንታ እና አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ ስምንት ግለሰቦች እና አምስት ኩባንያዎች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የተሻሻለውን የጉምሩክ አዋጅ 859/2006ን በመጥቀስ ከ20 በላይ የሚሆኑ ክሶች ሊቋረጡልን ይገባል በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ ምስከር የመስማቱ ሂደት ይቀጥል ብሏል።

ቀደም ሲል የተከሳሽ ጠበቆች ክስ ይቋረጥልን በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ አስመልክቶ ከህገ-መንግሰት አጣሪ ጉባኤ የተላከለት ውሳኔ ላይ ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ዛሬ ቀጠሮ ይዞ ነበር።

ተከሳሾቹ ለዚህ አቤቱታቸው መነሻ ያደረጉት በተሻሻለው አዋጅና በህገ-መንግስቱ ሁለት አንቀጾችን በመጥቀስ አዋጁና ህገ-መንግስቱ ተቃርኖ አላቸው የሚል ነበር።

ችሎቱ ይህንን አስመልክቶ ጉዳዩ ህገ-መንግስታዊ ትርጉም እንዲያገኝ ለህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ልኮ እንደነበርና ጉባኤው አይቃረንም የሚል ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል። ችሎቱ ከጉባኤው የተላከለት ውሳኔ ላይ ዛሬ ብይን በመስጠት ምስክር የመስማቱ ሂደት እንዲቀጥልም ትእዛዝ ሰጥቷል። በዚህም መሰረት እስከ ህዳር ወር መጨረሻ አቶ መላኩ ፈንታ እና አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ ያሉባቸው የመዝገብ ቁጥር 141352 እና 141356 ላይ የወጣውን የጊዜ ሰሌዳ አስታውቋል።

ሰኞ፣ ረቡዕ እና አርብ የአቃቤ ህግ ምስክሮች የሚሰሙ ሲሆን ማክሰኞ እና ሀሙስ በእነዚህ መዝገቦች ውስጥ በተከሳሾች የሚቀርቡ የተለያዩ አቤቱታዎች ብይን ሲሰጥባቸው ቆይተዋል። በመዝገብ ቁጥር 141354 ላይ ብይን ለመስጠትም ቀጠሮ ይዟል፡፡