አገር አቀፍ ዜናዎች

የጥቅምት 2-1-08

ከአንድ ዓመት በፊት በ47 ሚሊዮን ብር ካፒታል ወጭ የተቋቋመው ሽንትስ የጨርቃ ጨርቅ ጋርመንት ፋብሪካ መዳረሻውን በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በማድረግ የተለያዩ አልባሳትን እያመረተ ወደ አውሮፓ ሀገራት ይላካል፡፡

ድርጅቱ በኮሪያ ባለሃብቶች የተቋቋመና አፍሪካ ውስጥ የመጀሪያውን ፋብሪካ የከፈተው በአዲስ አበባ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ  ከ1,500 በላይ ሰራተኞች ቀጥሮ ያሰራል፡፡ ፋብሪካው የፈጠረው የስራ እድል መልካም ቢሆንም አብዛኞቹ ሰራተኞች ግን የወር ደሞዛቸው አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ደመወዛቸው ወቅቱን ጠብቆ እንደማይከፈላቸው ይናገራሉ፡፡ ይህ ደግሞ የቤት ኪራይን ጨምሮ ጊዜ ለማይሰጡ ወጭዎቻቸው ስለማይደርስ የተስተጓጎለ ህይወት እንድንመራ ተገድርጎናል ነው የሚሉት፡፡

ከደመወዝ መጠን ዝቅተኝነትና በወቅቱ ክፍያ ካለመፈፀሙ በተጨማሪ በየ 6 ወሩ የደሞወዝ ጭማሪ እንደሚደረግ ቢገለፅም በተግባር እየታየ ያለው ግን ወጥ ያልሆነና አንዳንዶች ከ6 ወር በፊት ጭማሪ ሲደረግላቸው አንዳንዶች ደግሞ በ10 ወርም ላይጨመርላቸው እንደሚችል አጨማመሩም ውጤቱን መሰረት ያላደረገ ነው ይላሉ፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የኢንዱስት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታደሰ ሃይሌ ችግሩ የደመወዝ ማነስ ሳይሆን ከተማው ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነት ነው ይላሉ፡፡

ይህንን ችግርም ለመቅረፍ ፋብሪካው እንደመፍትሄ እያሰበ ያለው የሰራተኞች መኖሪያ መንደር መገንባት ስለሆነ ለዚህ የሚሆን ቦታ ከመንግሥት ጠይቋልም ብለዋል፡፡ አቶ ታደሰ የደመወዝ በወቅቱ አለመክፈልን በተመለከተ የምናውቀው ነገር አልነበረም ችግሩ ካለ ግን እንከታተላለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

መስከረም 27/2008 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ነሐሴ 7 ቀን 1927 ዓ.ም ልዩ ስሙ ኦርማ ጋራዥ አካባቢ የተወለዱት አምባሳደር ዘውዴ ትምህርታቸውን በሊሴ ገብረማርያም ለ12 ዓመታት ከተማሩ በኋላ ወደ ፈረንሳይ ሀገር በመሄድ ተምረው በጋዜጠኝነት በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ ወደ ሃገር ከተመለሱም በኋላ በተለያየ የጋዜጠኝነትና በዲፕሎማትነት ሙያ አገልግለዋል፡፡  በጊዜውም የወሬ ምንጭ የሚባል የዜና አገልግሎት መስርተው ከዋና ዳይሬክተርነት እስከ ረዳት ሚኒስትርነት ደረጃ ያገለገሉ ሲሆን በፈረንሳይ የአምባሳደር ምክትል፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ረዳት ሚኒስትር፣ በሮም የንጉሠ ነገስቱ አምባሳደር እና በቱኒዚያ አምባሳደር ሆነው መስራታቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ በደርግ የስልጣን ዘመንም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ የዓለም አቀፍ የእርሻ ልማት ፈንድ መስሪያ ቤት የመንግስታት ግንኙነትና የፖለቲካ ኃላፊ በመሆን ለረጅም አመታት አገልግለዋል::

አምባሳደር ዘውዴ ጡረታ ከወጡ በኋላ በታሪክ ተመራማሪነት እና በጸሐፊነት ጊዜያቸውን ያሳለፉ ሲሆኑ ”የኤርትራ ጉዳይ በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት”፣ “ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ” እና “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ታሪክ” ካሳተሟቸው መጻህፍት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ መንግስት ሁለተኛ መጽሀፍንም እያዘጋጁ ነበር፡፡
አምባሳደር ዘውዴ ረታ በተወለዱ በ81 ዓመታቸው ማረፋቸውን ለአምባሳደሩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ገልፀዋል፡፡

መስከረም 20/2008 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲቲዩት የቀጣይ ጊዜ እቅዴ ናቸው ካላቸው መካከል በአዲስ አበባ ብቻ የነበረውን የካይዘን ተቋም ወደ ክልሎችም ማስፋፋት አንዱ ነው፡፡ በካይዘን ኢንስቲቲዩት የቆዳና ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሰብለ ወንጌል ሀረገወይን ለዛሚ እንደተናገሩት በተለይም ቀጣዩ 2016 የፈረንጆቹ ዓመት ሲመጣ ክልሎች ላይ የላቀ ስራ መስራት እንፈልጋለን፤ ዝግጅቱም ተጠናቋል ያሉ ሲሆን ይህ ከመንግሥትም የመጣ መመሪያ ነው ብለዋል፡፡

በካይዘን ፍልስፍና መሰረት የክልሎችን አቅም መገንባትና ያላቸውን ሃብት በትክክል ወደ ተግባር ለውጠውት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻልም ጭምር ይህ ስራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ሲሉ ዳይሬክተሯ ገልፀዋል፡፡ አማራና ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በጥቅሉ አራት ክልሎች ላይ ስራው የሚጀመር ሲሆን ቀስ በቀስም ወደ ሁሉም ክልሎች እንደሚቀጥል ተነግሯል፡፡

መስከረም 20/2008 ዓ.ም

ከፌዴራል የተነሱ 41 አርቲስቶችና 67 የሚዲያ ባለሞያዎች ተካተዋል፡፡ ከክልል የሚቀላቀሉ ሌሎች የታሪካዊው ጉዞ ተሳታፊዎችም ይጠበቃሉ፡፡ መነሻውን ባህር ዳር ያደረገው ይኸው ታሪካዊ ጉዞ መዳረሻውን ሃሙሲት በለሳ ጎንደር እና ዋግ ሁምራ ያደርጋል ተብሏል፡፡ ይሄው የጥበብ ጉዞ ለ35ኛ ጊዜ የሚከበረው የብአዴን ኢሀዴግ የምስረታ በአል አንዱ አካል ሲሆን በአሉ በድምቀት ህዳር 11 ይከበራል፡፡ የታሪካዊው ጉዞ ተሳታፊዎች ዛሬ ሃሙሲትና በለሳን ከጎበኙ በኋላ በሁለት ምድብ ተከፍለው ግማሹ ወደ ጎንደር እና ሌላኛው ምድብ ደግሞ ወደ ዋግ ሁምራ እንደሚያቀና ይጠበቃል፡፡ ይኸው “ታሪካዊ የጥበብ ጉዞ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ጉብኝት ዋነኛ መዳረሻዎቹም የብአዴን ኢሀዴግ የተመሰረተባቸውን እና የትጥቅ ትግል ያከናወነባቸው ቦታዎችን ያከተተ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡ ተጓዦቹም ለጉዞ የሚሆኑ የቀደምት ታጋዮች ይለብሷቸው የነበሩ ካኪ ቁምጣና ኮት እንዲሁም ሽርጥ ተሰጥቷቸዋል፡፡ (እንየው ቢሆነኝ)

መስከረም 18/2008 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ሽልማቱን ያገኘችው የምዕተ ዓመቱን ግቦች በማስፈፀም ረገድ ባስመዘገበችው ውጤት ነው፡፡ የዋንጫ ሽልማቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ተቀብለዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ኒዮርክ በተዘጋጀው በዚህ ስነ-ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ንግግር አድርገዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባንኪሙን ለተሸላሚ ሀገራቱ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ በቅርቡ ከዓለም ምግብ ድርጅት ዓለም አቀፍ ሽልማት እንደተበረከተላት ይታወሳል፡፡

መስከረም 18/2008 ዓ.ም

በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ የተወለደበትን ዕለት ምክንያት በማድረግ የሚከናወነው የመታሰቢያ ፕሮግራም ትናንት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በድምቀት ተከብሯል፡፡ ዘንድሮ ከክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰ ህልት በኋላ ለ7ኛ ጊዜ የተከበረው ይህ ዓመታዊ በዓል በብሔራዊ ቴአትር አዘጋጅነት ሲካሄድ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ከዚህ ቀደም በጥላሁን ስም የተቋቋመው ኮሚቴ ያዘጋጀው እንደነበር ተነግሯል፡፡

በዕለቱ ጥላሁንን የተመለከቱ የተለያዩ ትውስታዎችና ፁሁፎች እንዲሁም ስራውን የተመለከቱ ንግግሮች የቀረቡ ሲሆን የሙዚቃ ባለሞያና መምህር የሆነው አክሊሉ ዘውዴ ‹‹ጥላሁን በሙዚቀኛ አይን›› በሚል ርዕስ የጥላሁንን የድምፅ አወጣጥና የስራዎቹን ረቂቅነት ተናግሯል፡፡

1933 ዓ.ም ላይ የተወለደው ክቡር ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ 2001 ዓ.ም ላይ ህልፈቱ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ (ያልፋል አሻግር)

መስከረም 11/2008 ዓ.ም

ብሩክ ዘአብ ይባላል፤ የ15 ዓመት ታዳጊ ነው፡፡ የተወለደው በጎንደር ከተማ ቀበሌ 02 ሲሆን ከልጅነቱ ጀምሮ ፈጣን አዕምሮ እንዳለው በቅርበት የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ በጎንደር አካባቢ እና በሌሎች ስፍራዎች ያገኛቸውን መረጃዎች በቀዳሚነት ያሰራጫል፡፡

የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ቱሪስቶች ወደ ጎንደር ከተማ ሲገቡ ታሪካዊ ቦታዎችን ያስጎበኛል፤ የእንግዳ ማረፊያዎችንም ይጠቁማል፡፡ በዚህ በሚያገኘው ገቢ ትምህርቱን ይከታተላል፡፡ አሳዳጊ አያቱንም ይጦራል፡፡

በጎንደር አካባቢ ለመረጃ ካለው ቅርበት እና ፍጥነት ቢቢሲ የተሰኘውን ቅፅል ስም አግኝቷል፡፡ ለጎንደር ፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብም የህዝብ ግንኙነት ስራ ይሰራል፡፡ ሁሉም የጎንደር አካባቢ ነዋሪዎች ብሩክ ከማለት ይልቅ ቢቢሲ በማለት ሲጠሩት ይስተዋላል፡፡

በቅርቡ ወደ ጎንደር ተጉዘው የነበሩት የቢቢሲ ጋዜጠኞች ብሩክን ያገኙት ሲሆን በፍጥነቱና ለመረጃ ባለው ቅርበት ተደምመዋል፡፡ በቀጣይም መጥተው እንደሚያገኙት እና ልዩ ዘገባ እንደሚሰሩለት ቃል ገብተውለታል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

መስከረም 07/2008 ዓ.ም

በትናንትናው እለት በሸራተን አዲስ ሆቴል የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ለፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ለኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታደሰ ሃይሌ፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ደዋኖ ከድር እንዲሁም ለንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትር ከበደ ጫኔ በአማካሪያቸው በአቶ አየነ ፈረደ በኩል ከምክር ቤቱ ጎን በመቆም የግሉ ዘርፍ ለሚያጋጥመው ችግር መፍትሄ በመስጠታቸው የውጪውን ባለሃብት ከሀገር ውስጥ ባለሃብት ጋር ለማገናኘት ባደረጉት ጥረት ከወርቅ የተሰራ የምክር ቤቱ አርማ እና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በተጨማሪም ለኩላሊት እጥበት ማህበር የ100,000ሺ ብር ቼክ ስጦታ ለመስጠት አስተባባሪ አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ ከፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ለመቀበል ወደ መድረክ የቀረበ ቢሆንም ቼኩ በመረሳቱ ለሌላ ቀን በፕሬዝዳንቱ በኩል እንደሚደርስ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ ገልፀው አስተባባሪው ወደ መቀመጫው ተመልሷል፡፡ (ታሪክ አዱኛ) 

መስከረም 06/2008 ዓ.ም

ባለስልጣኑ አዳዲስ መንገዶችን ተከትለው የሚገነቡትን የህንፃ ባለቤቶች ህንፃቸውን ለመገንባት አሸዋና ጠጠሮች በእግረኛ መንገድ ላይ በማድረግ ችግር ስለፈጠሩ መንገዴን ሰርቃችኋል በማለት ቀጥቷቸዋል፡፡ በተሽከርካሪ መንገድ ላይ ለረጅም ጊዜ መኪና ማቆም፣ የጎዳና ላይ ንግድ እና ሌሎችም መንገዴን ተሰርቆብኛል እንድል ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው ብሏል፡፡ በመሰል ተግባር መንገዶቼን የሚሰርቁትን አሁንም ተከታትዬ መቅጣቴን እቀጥላለሁ ብሏል፡፡ (ነጋሽ በዳዳ)

መስከረም 06/2008 ዓ.ም

በየካ ሀያት ቁጥር 2 ኮንደሚኒየም አካባቢ እዮብ እንግዱ የተባለው የ3 ዓመት ህፃን አባቱን ጁስ ግዛልኝ ብሎ ይጠይቀዋል፤ አባትም ልጁ እዛው እንዲጠብቀው እና ገዝቶለት እንደሚመጣ ትዕዛዝ ሰጥቶ ጁሱን ሊገዛ አቅራቢያው ወዳለ ሱቅ ይሄዳል፡፡ ህፃን እዮብ አባቱን ከኋላ በመከተል ድንገት በአካባቢው በነበረና ተቆፍሮ ባልተደፈነ የውሀ ጉድጓድ ውስጥ ይገባል፣ አባትም ጁሱን ገዝቶ ሲመጣ ልጁን ከስፍራው ያጣዋል፡፡ ከ5 ደቂቃዎች በላይ በተደረገ አሰሳም ህፃን እዮብ እንግዱ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ተገኝቷል፡፡ ወደ ሆስፒታል እየተወሰደ በነበረበት ሰዓትም ህይወቱ አልፏል፡፡ 

መስከረም 06/2008 ዓ.ም

ሰሎሜ ጉልላት የተባለችው የ20 ዓመት ወጣት ከአንድ ሴት ከጓደኛዋ ጋር በመሆን በለቡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ በሚገኝ መዝናኛ ቤት በመዝናናት ላይ እያሉ በጥበቃ ስራ ላይ የነበረ የፌዴራል ፖሊስ አባል ከጓደኛዋ ጋር የመዝናኛው መፀዳጃ ቤት ሲገቡ ተከትሎ በመግባት የዋና ክፍሉን በር ቆልፎ በክፍሉ ውስጥ እንዳለች የተኩስ ድምፅ የተሰማ ሲሆን ወዲያው ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል፡፡ ተጠርጣሪው የፌዴራል ፖሊስ ባልደረባ ራሱን ለማጥፋት ቢሞክርም ሕይወቱ ባለማለፉ የሕክምና ዕርዳታ እየተደረገለት እንደሚገኝና ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ለዛሚ 90.7 ገልጧል፡፡

መስከረም 04/2007 ዓ.ም

አቶ ሞላ አስገዶም የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር እና ከመሰረቱ ነባር አባላት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ንቅናቄው በወቅቱ ስለተመሰረተበት እንዲሁም ስለተቋረጠበት ሁኔታ፤ በአሁኑ ወቅት በኤርትራ ውስጥ ስላለው እንቅስቃሴ በተጨማሪም በቅርቡ አሸባሪው ግንቦት ሰባት እና አርበኞች ግንባርን ጨምሮ ስላካሄዱት ጥምረት ዛሬ በግዮን ሆቴል መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ከግንቦት ሰባቱ መሪ ዶ/ር ብሀኑ ነጋ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት እንዲሁም አቶ ሞላ የጥምረቱ ምክትል ሊቀመንበር በቅርቡ መደረጋቸውን ተከትሎ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ በቃላቸው የማይገኙ ውሸታም ናቸው ሲሉ ገልፀዋቸዋል፡፡

ትግላቸውን ለማቋረጥ የተገደዱትም ኢትዮጵያ እያደገች በመምጣቷ በልማት መገስገሷ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለአንድ ዓመት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሲሰሩ እንደቆዩ የገለፁት አቶ ሞላ አስገዶም ባደረጉት እንቅስቃሴም የኤርትራ ወታደሮችን በመደምሰስ ወደ ሱዳንና ኢትዮጵያ መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

መስከረም 04/2008 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘት ከቀረቡት 3000 ያህል መስፈርቶች 40 ያህል ብቻ እንደቀረውና በተሰጠው ውስን ጊዜ ውስጥ ቀሪ መስፈርቶቹን አሟልቶ ሰርተፍኬቱን እንደሚያገኝ ተነግሯል፡፡ ዝቅተኛው የባቡር መስመር ዋጋ 2 ብር ሲሆን 4 ኪ.ሜ ወይም የ2 ብር መንገድን ሳይከፍል ለመጓዝ የሚሞክር የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ተጠቃሚም የዋጋውን 10 እጥፍ እንደሚከፍል ተገልጧል፡፡ 

መስከረም 2/2008 ዓ.ም

ራሱን የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) እያለ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን  ከሌሊቱ 6 እጁን ለመከላከያ ሰራዊታችን ሰጠ፡፡ ይህ ቡድን በሱዳን በኩል የገባ ሲሆን መተማ ላይ 700 ሰራዊቶች ሁመራ ላይ ደግሞ 100 ሰራዊቶች ከነትጥቃቸው ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እጃቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከመተማ ከተማ ነዋሪዎችም አቀባባል ተደርጎላቸዋል ሲሉ የአማራ ክልል ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገልጸዋል፡፡  11 መኪና ተጭነው እንዲሁም አንድ ኦራል የጦር መሣሪያ የጫነ ተሽከርካሪያቸውም መግባቱም ለዛሚ 90.7 ኤፍኤም ነግረዋል፡፡ ቡድኑ በኤርትራ መንግስት ድጋፍ የሚደረግለት ሲሆን በኢሳያስ አፎርቂ እንደ ቀኝ እጅ የምቆጠር መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል፡፡ 

ነሐሴ 29/2007 ዓ.ም

ተከሳሽ መሀመድ ሱልጣን  በሀምሌ 15/2007 ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ሲሆን በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ቀበሌ 04/06 ክልል ልዩ ቦታው አብነት በቀድሞው 36 ቀበሌ መዝናኛ ክበብ እየተባለ ከሚጠራው ቦታ የግል ተበዳይ የሆነችውን ወ/ሪት “ትርፍ ነሽ ውረጂ” በማለት በሀይል ጎትቶ ከተቀመጠችበት የሚኒባስ ታክሲ ወንበር ላይ በማውረድ በቀኝ እጁ አንድ ግዜ ሰንዝሮ  የፊት ለፊት የተፈጥሮ ጥርሷ እንዲወልቅ እና  ከመሀል ወደ ቀኝ ያለው ጥርስ  እንዲሁም ከመሀል ወደ ግራ ያለው ሁለተኛው ጥርስ እንዲነቃነቅ በማድረጉ  በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ  555(ለ) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ታስቦ በሚፈፀም ከባድ የአካል ጉዳት ወንጀል ተከሷል፡፡

ክሱን የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 11ኛ ወንጀል ችሎት አቃቢ ህግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሹ ጥፋተኛ ነው በማለት በ2 ዓመት ከ9 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)

ነሐሴ 28/2007 ዓ.ም

የኖርዌይ ዜግነት ያላቸው የሒልተን አዲስ አበባ ስራ አስኪያጅ ዛሬ ሰባት ሰዓት ላይ ምሳ ከሚበሉበት የሒልተን ጋዜቦ ሬስቶራንት በፖሊስ ተይዘው ተወስደዋል፡፡ ዋና ስራ አስኪያጁ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ሒልተን ውስጥ ከሚሰራውና ቢሮ ሆቴል ውስጥ ከሚገኘው እንጦጦ ትራቭልስና ቱርስ ጋር በተፈጠረ የውል ማክበርና ማፍረስ ጥያቄ እንደሆነ ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡ ክስ የተመሰረተባቸውም የእንጦጦ ትራቭልስና ቱርስ ከፍ/ቤት ተይዘው ይቅረቡ የሚል ማዘዣ በማምጣቱ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የክስ ጭብጡም እንጦጦ ትራቭልስና ቱርስ የሒልተን ሆቴል እንግዶች የሚጓጓዙበት አገልግሎት የሚሰጡ መኪናዎችን ለማቅረብ ከሆቴሉ ጋር ስምምነት ፈፅሞ እያለ ሆቴሉ በዋና ስራ አስኪያጁ አማካኝነት ከሌላ አቅራቢ ጋር ውሉ ሳያልቅ ስምምነት መፈፀማቸው እንደሆነ የደረሰን ጥቆማ ያመለክታል፡፡

ይህንን በውል ላይ የተፈፀመ ውል አግባብ አይደለም በማለት በፍ/ቤት የእግድ ትዕዛዝ ያወጣው የእንጦጦ ትራቭልስና ቱርስ እገዳው ስላልተፈፀመለት ለፍ/ቤቱ ባቀረበው ድጋሚ አቤቱታ ዋና ስራ አስኪያጁ ተይዘው ይቅረቡ የሚለው የፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሊተላለፍ መቻሉን በቦታው የነበሩ ምንጮች ገልፀዋል፡፡

ምንጮቻችን አያይዘውም የህግ አስከባሪ ሆነው በቦታው የፍ/ቤቱን ትዕዛዝ ሊያስፈፅሙ የመጡ የፖሊስ አባላት ለገፅታም ሆነ ለባህል በማይመጥን መልኩ ግለሰቡ ምሳቸውን እየበሉና ሌሎችም ተመጋቢዎች ባሉበት ጠረጴዛቸውን ከበው መቆማቸው ብዙዎችን እንዳሳዘነ፤ በተመሳሳይ የዲፕሎማቲክ ከለላ የሌላቸው የሆቴሉ ዋና ስራ አስኪያጅ የሀገሪቱን ህግ አክብረው እና ተቀብለው ከመሔድ ይልቅ በእብሪተኝነት የህግ አስከባሪዎችንም ማስጠበቃቸው ተገቢ አለመሆኑን አያይዘው ገልፀዋል፡፡ 

የዛሚ ሪፖርተሮች ስለ ጉዳዩ ለማጣራት ወደ ስፍራው ቢያቀኑም ሁለቱም ወገኖች ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ በእንጦጦ ትራቭልስ እና ቱርስ በኩል ስራ አስኪያጁ የሉም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ነሐሴ 27/2007 ዓ.ም

የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚንስቴር ሚንስትር ክቡር አቶ መኩሪያ ሀይሌ እንደተናገሩት ከመኖሪያ ቤቶች ዋጋ ጋር በተገናኘ እየተነሳ ያለው የዋጋ ጥያቄን ለመመለስ ሲባል ከአሁን በፊት የተመዘገቡ ሰዎች ከአቅማቸው ጋር የተመጣጠነ ማስተካከያ ለማድረግ ያስችላቸዋል፡፡ በዚህ መሰረት 40/60 የተመዘገቡ ሰዎች ወደ 20/80 ወይም 10/90 መቀየር ይችላሉ፡፡ አልያም ከ10/90 ወደ 20/80 እንዲሁም ወደ 40/60 ቀይረው ተመዝጋቢዎች እንደአቅማቸው መመዝገብ እንዲችሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡ (መሰረት ሙሉ)

ነሐሴ 26/2007 ዓ.ም

ከአዳማ ቡና ነው በማለት ፍቃድ ሳይኖረው 460 ኩንታል ጤፍ ጭኖ ከገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን ተፈትሻ_ል የሚል እና የኢትዮጵያ የቡና ጥራት ሀሰተኛ ማረጋገጫን በመያዝ  በቮልቮ  ኮድ 3/ 00265  ተሳቢ እና በኮድ 3/01111 ተሸከርካሪ ጭኖ ወደ ጅቡቲ መስመር ሲጓዝ የነበረው ተከሳሽ ሃይለማርያም ተክሉ ኤርሙካሌ ላይ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

ተከሳሹም በፈፀመው ወንጀል በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ድሬዳዋ ምድብ ወንጀል ችሎች ጥፋተኛ ተብሎ በ10 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል፡፡

በተጨማሪም 460 መቶ ኩንታል ጤፍና በእጁ ላይ የተገኘው 4.700  የአሜሪካ ዶላር ለመንግሥት ገቢ ተደርጓል ሲሉ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ሰለሞን አያሌው ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ገልፀዋል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)