አገር አቀፍ ዜናዎች

የአፍሪካን ልማት ባንክ ለደቡብ ሱዳን ድርቅን እንከላከል በሚባለዉ የአጭር ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ መፍትሄ ሰጭ በሆነዉ ፕሮጀክት በኩል ለደቡብ ሱዳን አርባሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ሰጠ፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ ከደቡብ ሱዳን እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር ድርቅን እንከላከል በተባለዉ ፕሮጀክት ስር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ይህም ዉል ድርቅን እንከላከል በተባለዉ ፕሮጀክት ስር በአፍሪካ ልማት ባንክ ቦርድ ዳይሬክተሮች አማካኝነት እ.ኤ.አ ጁላይ 21 2017 የፀደቀ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ድርጅትም በደቡብ ሱዳን በወኪሉ አማካኝነት ይህን በተግባር ላይ ለማዋል የሚከናወኑ ነገሮችን እየተከታተለ ሪፖርት እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡ወኪሉም ከመንግስታት ጋር በመተባበር እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡
የባንኩ አላማም ሶስት መቶ ሺ ለሚደርሱ የደበብ ሱዳን ግለሰቦች ድርቁን በአስቸኳይ ለመቋቋም የሚያስችሏቸዉን መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማለትም ምግብ ፣ ዉሀ እንዲሁም የህክምና አገልግሎቶች ማቅረብ እንደሆነ ተናግሯል፡፡በተጨማሪም በምግብ ለተጎዱ ሌሎች አካላትም እንደሚረዱ ጨምረዉ ገልፀዋል፡፡
የእርዳታዉም ስምምነት በዋነኝነት በሶማሊያ እና በደቡብ ሱዳን እጅጉን ለተጎዱ ህዝቦች የምግብ እና የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ነዉ፡፡
ይህ ባንክ በድርቅ ለተጎዱ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሀገራት 1.1 ቢሊዮን ብር ለመስጠት አቅዷል፡፡
በፊርማዉ ሰአትም የቦርዱ አባላት እና የተለያዩ ባለስልጣናት እየሆነ ባለዉ ነገር ደስተኛ መሆናቸዉን ገልፀዋል በተጨማሪም ይህ ድጋፍ የደን የግብርና እና ተመሳሳይ የሆኑ የሚኒስተር መስሪያ ቤቶችን እንዲጠነክሩ ያደርጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ምንጭ ሱዳን ትሪቡን

በ6ክልልሎች የሚገኙ 8.5 ሚሊየን ህዝቦች የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸዉ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል 3.67 ሚሊየን ተጎጂዎችን በመያዝ ከፍተገኛዉን ቁጥር ይዟል፡፡ ለአጠቃላ ተጎጅዎችም እርዳታ 487.7 ሚሊየን ዶላር ያስፈልጋል፡፡
በበልግ አብቃይና በአርብቶ አደር አከባቢዎች በተደረገ የምግብ ዋስትና የዳሰሳ ጥናት ለቀጣይ አምስት ወራት ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊየን ህዝብ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልገዉ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገልጻዋል፡፡
የተረጂዎች ቁጥርም ባለፈዉ አመት ከነበረዉ ሰባት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ወደ ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊየን የጨመረ ሲሆን ለዚህም ምክንያት ናቸዉ የተባሉት
የበልግ ዝናብ መዛባት፤ የመኖና ግጦሽ ማነስ፤ የምርት መቀነስና የዉሀ እጥረት ተጠቅሰዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል በ ሶስት ነጥብ ስድስት ሚለየን ተጎጂ በመያዝ በተጎጂ ቁጥር ቀዳሚ ሆናለች፡፡
ለተጎጂዎች እርዳታ አራት መቶ ሰማንያ ሰባት ሚሊየን ሚሊየን ነጥብ ሰባት የአሜርካን ዶላር እንደሚያስፈልግ የገለፀዉ ኮሚሽኑ የኢትዮጲያ መንግስት ለዚህ እርዳታ ከስድስት መቶ ሰባ ሁለት ሚሊየን ብር በላይ በመመደብ የእህል ግዥ በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቴር የሆኑት አቶ ደበበ ዘዉዴ ለዛሚ ተናግረዋል፡፡
ትብለጽ ተስፋዬ ዘግባዋለች፡፡

ንፋስ የቀላቀለ ከፍተኛ ዝናብ ተከስቶ የወደቀ ዛፍ ሁለት መኪኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፡፡
በአዲስ አበባ በተለምዶ ፍልውሃ እየተባለ በሚጠራው አከባቢ ከፍተኛ ንፋስ ቀላቅሎ በጣለ ዝናብ ምክንያት 96907 ታርጋ ቁጥር አ.አ የተመዘገበ ሀይሎክስ መኪና ላይ ዛፍ ወድቆበት ከጥቅም ውጪ ሆኖል፡፡
በተጨማሪም እዛው የቆመ የቤት መኪና ታርጋ ቁጥር 974220 የተመዘገበ የሆላ መስታወቱ ሙሉ በሙሉ ረግፎል ፡፡
አደጋው የተከሰተው ሀይለኛ ዝናብ በመዝነቡ ምክንያት እና ከፍተኛ ዝናብ በመኖሩ እንደሆነም በቦታው የነበሩ የአይን እማኞች ገልጸውልናል፡፡
ግዙፉ ዛፍ ከስሩ ተነቅሎ መኪናው ላይ በመውደቁ መኪናው ከአገልግሎት ውጪ እንደሆነም መመልከት ችለናል ፡፡
በቦታው የትራፊክ ፖሊሶች እንዲሁም የከተማው ፖሊሶች የነበሩ ቢሆንም አደጋውን መከላከል አልተቻለም ፡፡
ዛፉ የመኪና አሰፋልት ላይ በመውደቁ መንገዱ በጣም ተጨናንቆ የነበረ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች በመተባበር ዛፉን ከወደቀበት ለማንሳት ጥረት እያደረጉ እንደነበር በቦታው ተገኝታ ፍሬህይወት ታደሰ ዘግባዋለች፡፡

ከ59ሺህ በላይ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዩች ውስጥ በቀን ገቢ ግምቱ ዙሪያ 24 በመቶው ብቻ ቅሬታ ቢያቀርቡም ባለስልጣኑ የክፍያው ሂደት በዚህ ምክንያት ተጓቷል ሲል የመክፈያ ቀነ ገደቡን ለ10 ቀናት አራዘመ፡፡
የኢትዮጲያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የቀን ገቢ ግምትን አስመልክቶ ከማህበረሰቡ ያሰባሰባቸዉን የህዝብ ቅሬታና አስተያየት መሰረት በማድረግ ሀምሌ 18 ቀን 2009 አ.ም በሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ቅሬታ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ እንደተፈታና ከ 59ሺ 275 የደረጃ ሐ የግብር ከፋዮች መካከል ቅሬታ ያቀረበዉ 24በመቶዉ የሚሆነዉ ብቻ መሆኑን የገለጸዉ ባለስልጣኑ ቅሬታቸዉንም 99.2በመቶ ፈትቻለሁሲል አሳውቆ ነበር፡፡
ታዲያ የ2009 ግብር ማሳወቂያ ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. መጠናቀቅ ቢኖርበትም በቀን ገቢ ግምት መረጃ አሰባበሰቡ ዘግይቶ በመጀመሩ በርካታ ግብር ከፋዮች ጊዜው እንዲራዘም ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ ባለስልጣኑም ግብርን አሳውቆ የመክፈያ ጊዜው እስከ ነሃሴ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ለ 10 ቀናት አራዝሟል፡፡ በተለያየ ጊዜ ከህዝቡ የተነሱ ቅሬታዎችንና የባለስልጣኑን ምላሽ በምሽት የዛሚ 24 አቅርቦ እንደነበር የሚታወስ ነዉ፡፡
ትብለፅ ተስፋዬ ዘግባዋለች፡፡

ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ 573/2000 ላይ በሚያደርጉት ድርድር የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሲሳተፉ የሚያስፈልጋቸው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፊርማ ብዛት ከፍ እንዲል ተስማሙ፡፡
በዛሬው እለት በአዋጁ ላይ መጨመር እና መቀነስ እንዲሁም መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ የተወያዩት የፓለቲካ ፓርቲዎች ለእለቱ ካነሷቸው ጉዳዩች መካከል የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድምጽ ብዛት ላይ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
በዚህም መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሲሳተፉ የሚያስፈልጋቸው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፊርማ ብዛት በሀገር አቀፍ ደረጃ መወዳደር የሚፈልግ ፓርቲ ያስፈልገው የነበረው የ1ሺህ500 ሰዎች ፊርማ ወደ 3000 እንዲሁም በክልል ደረጃ 750 የነበረው ወደ 1ሺህ500 እንዲያድግ ፓርቲዎቹ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የድርድሩ የሚዲያና ኮሚዩንኬሽን ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ባለፉት ሁለት መድረኮች ባደረጉት ድርድር ከአዋጁ ውስጥ የመጀመሪያዎቹን 31 አንቀፆች ተወያይተውባቸዋል፡፡
በአዋጁ ላይ የሚደረገው ውይይት ሲጠናቀቅ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን ነጥቦች ለህዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
የፓለቲካ ፓርቲዎቹ ለመደራደር የሚሆኑ ጉዳዩች እና ቅደምተከተላቸው ላይ ሲደራደሩ ከስድስት ወራት በላይ ከፈጀ በኋላ ይህ ድርድር በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ናርዶስ ዩሴፍ

የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ከማስታወቂያ ጀምሮ ባሉ ከአንድ ሺህ በላይ ጉዳዩች ላይ የሚያወጡትን አላስፈላጊ ወጪ እንዲያቆሙ አስጠነቀቀ፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለ2010 የበጀት አመት 320.8 ቢሊዩን ብር ለኢፌድሪ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አቅርቦ ያጸደቀ ሲሆን የተለያዩ የመንግስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ገንዘብ በማፍሰስ በማስታወቂያ መስሪያ ቤቶቻቸውን ለማስተዋወቅ፤ አላስፈላጊ የሆነ በሚል ያስቀመጠውን ለስብሰባ የሚወጣ ከፍተኛ አበል ፤ ለተለያዩ ጉዳዩች የሚፈጸሙ የአበል ክፍያዎች እጅግ ከፍተኛ መሆን እና ነዳጅ አጠቃቀሞችንም የሚጨምር ከአንድ ሺህ በላይ ጉዳዩች የተካተቱበት ዝርዝር በማዘጋጀት ለሚኒስትር መስሪያ ቤቶቹ የገንዘብ አጠቃቀማቸውን ወጪ ቆጣቢ እንዲያደርጉ አሳስቦ አሰራጭቷል፡፡
ከእነዚህ መስሪያ ቤቶች መካከል የፌደራል የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለአመራር እና ድጋፍ አገልግሎት ፕሮግራም 6 ሚሊየን 107 ሺህ 172 ብር የተመደበለት ሲሆን ይህ ገንዘብ ለአበል እና ለስልጠና ወጪ የሚደረግ ነው፡፡
የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ ለዛሚ እንደተናገሩት መስሪያቤቶቹ እንዲሰሩ የተሰጣቸውን ገንዘብ አላፈላጊ በሆነ ሁኔታ እያባከኑት እንደሆነ እና ከአትራፊ ድርጅት እኩል እራሳቸውን ማስተዋወቅም አላስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ ከሆነ መስሪያ ቤቶቹ በሬድዩ እና በቴሌቪዥን የሚያሰራጯቸው ማስታወቂያዎች እና ስፖንሰር የሚያደርጓቸው ፕሮግራሞች በቀጥታ እነሱን የሚመለከቱ ሆነው አልተገኙም ውጤት ተኮርም አይደሉም፡፡
ውጤት ተኮር ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት መስሪያ ቤቶች መካከል የኢትዩጲያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ስለ ግብር መክፈል የሚያስተላልፋቸው ዝግጅቶች ውጤት ተኮር የሆነ መስሪያ ቤቱ ገንዘብ አውጥቶ በሌላ መልኩ የሚያገኝበት ነገር ነው ሲሉ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬቱ ለዛሚ ተናግረዋል፡፡
በ2010 የበጀት አመት የኢትዩጲያ መንገዶች ባለስልጣን 50 ቢሊዩን ብር፤ በሁለተኛነት የትምህርት ሚኒስቴር እና በስሩ ያሉት ኤጀንሲዎች እንዲሁም የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ከ700 ሚሊዩን እስከ 1 ቢሊዩን ብር ድረስ ተመድቦላቸዋል፤ ግብርና እና መከላከያ እንዲሁም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ9 እስከ 12 ቢሊዩን ብር በሚደርስ በጀት ከፍተኛ ገንዘብ ከተመደበላቸው መካከል ናቸው፡፡
አቶ ሀጂ ታዲያ ሁሉንም መስሪያ ቤቶች ትልልቅ በጀት ከተመደበላቸው በተዋረድ እንደየጠቀሜታ ፈርጃቸው በጀት የጸደቀላቸውን መስሪያ ቤቶች የተመደበላቸው ገንዘብ ለስራ እንጂ አላፈላጊ በሆነ መልኩ መስሪያቤቱን ለማስተዋወቅ እና ገንዘብ ለማውጣት አይደለም ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ናርዶስ ዩሴፍ ዘግባዋለች

የአሜሪካ ተምች 32 በመቶ የሚሆነውን የኢትዩጲያ የበቆሎ ማሳ በማጥቃቱ የሀገሪቷ የዋጋ ግሽበት እንዲያሻቅብ አደረገ፡፡
ትላንት ባጠናቀቅነው የሀምሌ ወር የሀገሪቷ ወርሀዊ የዋጋ ግሽበት ወደ 9.4 በመቶ ማደጉን የማእከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የዋጋ ግሽበትን አጠቃላይ የሆነ የዋጋ መጨመር ወይም ደግሞ ብዙ ገንዘብ ትንሽ እቃ ሲፈልግ ማለት ነው ሲሉ ይተረጉሙታል፡፡
ባለፉት 10 ወራት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣው የዋጋ ግሽበት በጥቅምት ወር ከነበረበት 5.6 በመቶ አሁን ወደ ሁለት አሀዝ እድገት እጅጉን ተጠግቷል፡፡
የዋጋ ግሽበት ባለሁለት አሀዝ እድገት ማሳየት ያለውን ትርጉም የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ አክሊል ውበት የወጋ ግሽበት እድገት ኢኮኖሚው ሲያድግ ሊፈጠር የሚችል ነገር ቢሆንም ከነጠላ አሀዝ እድገት በአንዴ ወደ ባለሁለት አሀዝ እድገት ከተሸጋገረ በኢኮኖሚው የፍላጎት እና የአቅርቦት አቅም ላይ ክፍተት መኖሩን እንደሚያመላክት ለዛሚ ተናግረዋል፡፡
ግሽበቱ የተፈጠረው የእህል ዋጋ በተለይም የበቆሎ ዋጋ በመናሩ እንደሆነ ሲጠቀስ የምግብ ዋጋ ግሽበት በሰኔ ወር ከነበረበት 11.2 በመቶ ወደ 12.5 በመቶ አድጓል፡፡
በሀገሪቷ አብዛኛው ክፍሎች አዲስ አበባን ጨምሮ አንድ ኪሎ በቆሎ በ12 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት በኪሎ በ7 እና 8 ብር ሲሸጥ የነበረው ምርት አሁን ዋጋው እንዲያሻቅብ ሀገሪቷ ለመሰብሰብ ያቀደችው 30 ሚሊዩን ኩንታል በቆሎ በተከሰተው የአሜሪካ ተምች ምክንያት በበቆሎ ከተሸፈነው 71ሺህ 508 ሄክታር 32.2 በመቶው መውደሙ ግሽበቱ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡
በሀገሪቱ የሰብል ምርት ማሽቆልቆል የጀመረው ከባለፈው አመት ጀምሮ ሲሆን በወቅቱ የተሰበሰበው ምርት ከዚያ ቀደም ከነበረው አመት ማለትም በ2007 ከነበረበት በ4.8 ሚሊዩን ኩንታል ዝቅ ብሏል፡፡
ናርዶስ ዩሴፍ ዘግባዋለች፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ለተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከ200 በላይ የአሳንሰር ግዢ ጨረታ የተጫራቾች አቅም ከደረጃ በታች መሆን አዘገየ
በተለያዩ አካባቢዎች በከተማ አስተዳደሩ የአሳንሰር የይገዛልን ጥያቄ የቀረበባቸው ከሁለት መቶ በላይ አሳንሰሮች ወይም ሊፍቶች ግዢ ጨረታ ሲያካሂድ የነበረው የፌደራል ንብረት ግዢና ማስወገድ ኤጀንስ ጨረታው በወቅቱ ውድቅ የተደረገበትን ምክንያ ተጫራቾች በቴክኒክና በፋይናንስ ያሳዩት ብቃት ከደረጃ በታች በመሆኑ ነው ፡፡
ሜሪት እና ኮምፕሪናስ ቤዝድ የተጫቾቹ ቴክኒክ አቅም እና በፋይናንስ የተጫራቾቹ አቅም ቢፈተሸም በሁለቱም ዘርፍ ተጫራቾቹ ማሟላት ባለ መቻላቸው ጨረታው ውድቅ ተደርጓል፡፡
የንብረት ጊዢ አዋጅ ቁጥር 649 /2001 የፌደራል ንብረት ግዢና ማስወገድ ኤጀንሲ የፌደራል ባለ በጀት መስሪያቤቶች አቅም ይገነባል የመንግስት ንብረቶችን ያስተዳድራል በሻጭና በገዢ መካከል ያሉ አቤቱታዎችን ይፈታል ከክልሎች የሚመጡለትን የዕቃ ግዢዎች እንደሚያስተናግድ በግልፅ ተቀምጠዋል፡፡
አሁን ላይ የ202 አሳንሰሮችን የግዢ ጨረታ ከፌደራል ንብረት ግዢና ማስወገድ ኤጀንሲ ተረክቦ እየሰራ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንብረት ግዢና ማስወገድ ኤጀንሲ ሲሆን አሳንሰሮቹ የጨረታ ግዢ ሂደት ላይ መሆኑንና በመስከረም አሊያም ጥቅምት ወር ላይ ግዢያቸው ይፈፃማል ተብሏል፡፡

በአፋር ክልል በደረሰ ከፍተኛ ጎርፍ ሳቢያ 63 ሺህ ሰዎች አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡
በአፋር ክልል መጋሌ ወረዳ ዞን ሁለት በደረሰው የጎርፍ አደጋ 204 የሚደርሱ ቤቶች፣ትምህርት ቤቶች እና የህክምና ጣቢያዎች ችግር ገጥሞቸዋል፡፡ በክልሉ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ነዋሪዎቹ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ፣ የምግብ እጥረትም አጋጥሞቸዋል በተጨማሪም በዚህ ክረምት ብቻ 44 ሺህ አንድ መቶ ዜጎች ከቤታቸው እንደሚፈናቀሉ ተተንብዮል፡፡ ይህንን ችግር ተመልክቶ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለክልሉ በተለይም በወረዳዉ በድርቁ የከፍ ጉዳት በደረሰባቸው 15 ቀበሌዎች ለሚገኙ አንድ ሺ ያህል ነዋሪዎች 5ሺ ፍየሎች አከፋፍሎል፡፡ በባለፈው አመትም ከ2 ሺህ 3 መቶ በላይ የወረዳዉ ነዋሪዎች የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጎል፡፡ አፋር ክልል በከፍተኛ መጠን ጎርፍ ከሚያጠቃቸው ክልሎች ቀዳሚውን ስፍራ ስትይዝ እንደ ዋና ምክንያት ደግሞ የሚቀመጠው የአዋሽ ወንዝ በከፍተኛ መጠን መሙላት ነው፡፡ ሌላው ከፍተኛ ዝናብ ከከፍታማ የሀገሪቱ ክፍሎች ማለትም በአማራ እና በትግራይ ክልል መከሰት ለአፋር ክልል በጎርፍ መጥለቅለቅ ተጠቃሽ ምክንያት ናቸው ስትል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣውን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ
ፍሬህይወት ታደሰ ዘግባዋለች ፡፡

810 ግራም የኮኬይን እፅ በሆዱ ዉስጥ ይዞ የተያዘዉ ተከሳሽ በእስራት እና በገንዘብ ተቀጣ::
ተከሳሽ ሚስተር መላቼይ አኩቹኩዉ በፈፀመዉ የተከለከሉ ዕጾችን ማዘዋወር ወንጀል በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ የልደታ የወንጀል እና የፍትሐብሔር ፍትህ አስተዳደር ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬከቶሬት ዐቃቢ ሕግ በመሰረተዉ ክስ በእስራት እና በገንዘብ መቀጮ መቀጣቱን አስታወቀ::
የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳዉ ተከሳሽ የወንጀል ህግ አንቀጽ 525 /1/ለ ስር የተመለከተዉን በመተላለፍ ግንቦት 18 ቀን 2009 አመት ምህረት ከምሽቱ በግምት 3 ሰዓት ሲሆን ከብራዚል ሳኦወፖሎ ወደ ናይጀሪያ ሌጎስ ለመሄድ ቦሌ አየር መንገደ ለትራዚተ ባረፈበት ወቅት እንዳይመረት እንዳይዘዋወርና ጥቅም ላይ እንዳይዉል የታገደ የኮኬይን ዕፅ በሆዱ ዉጦ ለማለፍ ሲሞክር በተደረገ ፍተሻ ሀያ ዘጠኝ ፍሬ እጽ ከሆዱ ዉስጥ የወጣ ሲሆን በፌዴራል ፖሊሲ ኮሚሽን ለምርመራ ከሄደ በኃላ 15 ፍሬ ከሆዱ ወጥቷል ተከሳሽ አጠቃላይ 810 ግራም የኮኬይን እፅ በሆዱ ዉስጥ ይዞ የተገኘ በመሆኑ በፈፀመዉ መርዛማ እፆችን ማዘዋወር ወንጀል ተከሷል።
ለተከሳሹ ክሱ ደርሶት እና በችሎት ተነቦለት በአስተርጋሚ እየታገዘ እንዲረዳዉ ከተደረገ በኃላ የእምነት ክህደት ቃሉን እንዲሰጥ የተጠየቀዉ ተከሳሽ ያለምንም መቃወሚያ ድርጊቱን ፈፅሜለሁ ጥፋተኛ ነኝ ብሏል::
የፌዴራል ዐቃቢ ሕግ ለጉዳዩ ያስረዱልኛል ያላቸዉን የሰነድ ማስረጃ ካቀረበ በኋላ ተከሳሹ የወንጀል ድርጊቱን ፈፅሜለሁ በማለቱ ሌላ ማስረጃ መሰማት ሳያስፈልግ የጥፋተኝነት ዉሳኔ እንዲሰጥ የጠየቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን በመመልከት ተከሳሹን በተከሰሰበት ክስ ጥፋተኛ ነህ ብሎታል::
የቅጣት አስተያያት የተጠየቀዉ የፌዴራል ዐቃቢ ህግም የወንጀሉ አፈፃፀምና ይዞ የተገኘዉን የኮኬን ዕፅ መጠኑ ሲታይ ደረጃዉ መካከለኛ ተይዞ ተከሳሹን ሊያስተምር ሌሎችንም ሊያስጠነቅቅ የሚችል ቅጣት እንዲወሰን በማለት ሲያመለክት ተከሳሽ በበኩሉ በተከላካይ ጠበቃዉ አማካኝነት የወንጀል ድርጊቱን ማመኑ የቤተሰብ አስተዳዳሪ እና የወንጀል ሪከርድ የሌለበት መሆኑን በመጥቀስ በማቅለያነት እንዲያዝለት በማለት አመልክተዋል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 8ኛ ወንጀል ችሎት መዝገቡን መርምሮ ደረጃዉ በመካከለኛ በማለት መነሻ ቅጣት 10 አመት በመያዝ ግንቦት 14 ቀን 2009 አመት ምህረት በዋለዉ ችሎት በ7 አመት ጽኑ እስራትና በ7000 ብር የገንዘብ መቀጮ አንዲቀጣ ሲል ወስኗል::
የመረጃ ምንጭ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነዉ።

በአሁኑ ሰአት በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘዉን የአሜሪካ መጤ ተምች ለማጥፋት በዘርፉ ተመራማሪዎች የተለያዩ ሙከራዎች እየተደረጉ ባለበት ወቅት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የአሜሪካ መጤ ተምችን የሚያጠፋ ፀረ ተምች መድሀኒት ማግኘታቸዉን ይፋ አድርገዋል።
ተመራማሪዎቹ ይህ መጤ ተምች ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ምርምር መጀመራቸዉን እና ያገኙትን ጸረ ተምች መድሀኒት በወላይታ ዞን በሚገኙ የተወሰኑ ወረዳዎች ላይ ሙከራ አድርገዉ ጥሩ ዉጤት መገኘቱን በዩኒቨርስቲዉ የምርምር እና ማህበረሰብ ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ዶክተር ብርሃኑ ኩማ ለዛሚ ተናግረዋል።
በተለያዩ የማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ያገኙትን የጸረ ተምች መድሀኒት የባለቤትነት ማረጋገጫ እስካላገኙ ድረስ ለህብረተሰቡ ጥቅም ላይ እንደማያዉሉት እየተናገሩ እንደሆነ የሚገልጹ መልእክቶች እየተጻፉ ስለመሆኑ ከዛሚ ለተነሳላቸዉ ጥያቄም
ዶክትር ብርሀኑ መድሀኒቱ ስለተቀመመባቸዉ እጽዋቶች እንዲሁም ስለ ሂደቱ ለመናገር ተመራማሪዎቹ የፈጠራ ባለመብት መሆናቸዉ እንዲረጋገጥ እንደሚፈልጉ መናገራቸዉን እና ለዚህም እንቅስቃሴ መጀመራቸዉን ገልጸዉ
ከኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽ/ቤት ጋር በመነጋገርም የባለቤትነት ማረጋገጫ ምዝገባዉን ካደረጉበት እለት ጀምሮ ስራቸዉን መቀጠል እንደሚችሉ ስምምነት ላይ መደረሱን ነግረዉናል።
የኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ በበኩላቸዉ ምንም እንኳን የፈጠራ ባለመብትነት ሂደቱ ግዜ የሚወስድ ቢሆንም ከጉዳዩ አሳሳቢነት እና ሀገራዊ ፋይዳ አንጻር በልዩ ሁኔታ ታይቶ የምርመራዉ ጊዜ እንዲያጥር ሊደረግ እንደሚችል ለዛሚ ተናግረዋል።
ተመራማሪዎቹ ሀምሌ 24 ቀን ወደ ኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽ/ቤት በማምራት የባለቤትነት ማረጋገጫ ጥያቄያቸዉን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።
እጹብድንቅ ሀይሉ

ኢትዮጲያ ለደቡብ ሱዳን ስደተኞች 1 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ወጪ በማዉጣት ተጨማሪ የመጠለያ ጣቢያ ከፈተች፡፡
አዲስ የተከፈተዉ የስደተኞች ጣቢያ በደቡብ ሱዳን በተከሰተዉ አስከፊ የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ የሀገሪቱ ዜጎችን የሚያስተናግድ እንደሆነ ታዉቋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተገነባዉ ጣቢያ ስደተኞችን ለማስተናገድ ጤቀሜታዉ የጎላ እንደሆነና መጠለያ ጣቢያዉም በጋምቤላ ሸርቆሌ ያለዉን ዋነኛ የስደተኞች መቀበያ መጨናነቅ እና ጫናን እንደሚቀንስ ተገልፁል፡፡
እደተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ገለጻ ከሆነ በኢትዮጲያ ጋምቤላ የሚገኘዉ ጣቢያ ብቻዉን 285.809 የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል አጠቃላይ በክልሉ 7 የመጠለያ ጣቢያዎች ሲኖሩ 370.000 ስደተኞች አስጠልሏል ፡፡
እ.እ.አ 2011 ከሱዳን ነጻነቷን ያገኘችዉ ደቡብ ሱዳን ከ 2አመት ቆይታ በሃሏ እንደ እ.እ.አ 2013 በሀገሪቱ በተፈጠረዉ ቀዉስ ምክንያት ከ 2 ሚሊየን በላይ ዜጎች ለስደት ሲጋለጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል፡፡
ትብለጽ ተስፋዬ ዘግባዋለች

የአደጋ ጊዜ መውጫ ህግ ለሰባት ተከታታይ አመታት ለአዲስአበባ ምክርቤት ቢቀርብም ውሳኔ ባለመስጠት የከተማዋ ነዋሪዎች አደጋ ላይ መሆናቸውን የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች ባለስልጣን አረጋገጠ፡፡
የአደጋ ጊዜ መውጫ ደንቡ ከ2002 ጀምሮ የወጣ ቢሆንም እሰከአሁን ግን አልጸደቀም ምንም አስገዳጅ ህግ ባለመኖሩ የህንጻ ባለቤቶች ደግሞ ወጪ መቀነስ ላይ ትኩረት በመስጠት እንዲሁም የግንዛቤ እጥረት በመኖሩ በተጨማሪም በቸልተኝነት ይሄንን ችግር እየፈጠረ መሆኑ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ሲሉ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት የሆኑት አቶ ንጋቱ ማሞ ለዛሚ ገልጸዋል፡፡
በከተማው የሚታዩ ትልልቅ ህንጻዎች ጨምሮ መጓጓዣዎች የአደጋ ጊዜ መውጫ አይሰራለቸውም ምንአልባትም ቢሰራላቸው እንኳን ማህበረሰቡ ስለአጠቃቀሙ ያለው ግንዛቤ ተጨባጭ አይደለም፡፡
የአደጋ ጊዜ መውጫ በር አከባቢ የተለያዩ ቁሳቁሶች መቀመጥ እንደሌለበት ባለሞያው አክለው ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም በዚህ ጉዳይ ላይ መንግስት አስገዳጅ ደንብ መውጣት እንዳለበት እንዲሁም የሚመለከተው መስሪያቤት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ቢሰሩ የህንጻ ባለቤቶች ለራሳቸውም ለህብረተሰቡም ደህንነት ሲባል ህንጻዎች ሲያሰሩ የአደጋ ጊዜ መውጫ አስፈላጊነት ተረድተው ቢያሰሩ የተሻለ ለውጥ እንደሚመጣ አቶ ንጋቱ ማሞ ይናገራሉ፡፡
ዘገባው የፍሬህይወት ታደሰ ነው

የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ማዕከል በመዛኞች ጥራት ላይ ጉድለት እንዳለበት አመነ፡፡
በሀገሪቱ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ስርአትን ዋነኛ ግቡ ያደረገዉና በዝቅተኛና መካከለኛ ደረጃ ሙያተኞች በሚፈልገዉ ብዛት ፤ብቃትና ጥራት በራሱ የሚተማመንና ብቁ የሰዉ ሀይል የመፍጠር አላማን ያነገበዉ የሙያ ምዘናና ማረጋገጫ ማዕከል በመዛኞች ጥራት ላይ ጉድለቶች እንዳሉና በ2010 ይህንን ችግር ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት ማቀዱን በሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ወይንሸት ዘርይሁን ዛሬ ለጋዜጠኞ በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡
በ2000አ.ም ስራ የጀመረዉ የብቃትና ምዘናና ማረጋገጫ ማዕከል እስከ አሁን ድረስ ማለትም እስከ 2009 በጀት አመት ማጠቃለያ ድረስ 570.831 ተመዛኞች ወደ ተቋሙ በመምጣት 289.331 ብቃታቸዉን ማረጋገጣቸዉን ሪፖርቱ ዳሳል፡፡
በአዲስ አበባም 5 አከባቢዎች ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በመገናኛ ፤ በጎና ሲኒማ፤ በሰፈረሰላም፤ በልደታና አራት ኪሎ መክፈቱን ገልፆ የቅርንጫፎቹ መከፈት ለተመዛኞች የተቀላጠፈ መስተንግዶ ትልቅ አስተዋፅዎ እዳለዉም ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡
ትብለጽ ተስፋዬ ዘግባዋለች፡፡

የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለ 2010 የበጀት አመት ላስቀመጣቸው ግቦችና
ተግባራት በሚሰጣቸው ክብደት መለኪያ ከ 10 ሚሊየን ብር በላይ የተመደበለትን የፋይናንስ
ጉዳይ ከአጠቃላይ ጉዳዩች 10 በመቶ ክብደት ብቻ ሰጥቶታል፡፡
ኤጀንሲው ለፋይናንስ ጉዳዩች ለዘመናዊ እና ፍትሀዊ የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር
ፕሮግራም ማስፈጸሚያ 2 ሚሊዩን 7ሺህ 702 ብር፤ ዘላቂ የመፈጸም እና የማስፈጸም
አቅም መገንባት ፕሮግራም 2 ሚሊዩን 706 ሺህ 333 ብር እንዲሁም ለአመራር እና ድጋፍ
አገልግሎት ፕሮግራም6 ሚሊየን 107 ሺህ 172 ብር የተመደበለት ሲሆን በተጨማሪም
የኤጀንሲውን ግዢ አፈጻጸም በተዘጋጀው ቅድ መሰረት ስራ ላይ ለማዋልና ለፋይናንስ ግዢ
እና ንብረት አስተዳደር ውጤታማነትን ለማሻሻል በአጠቃላይ በበጀት አመቱ አፈጻጸም
የሚኖረው ድርሻ 10 በመቶ ሆኗል፡፡
በእቅዱ ላይ ለተገልጋይ ማለትም የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እና የኤጀንሲው ሰራኞችን
እርካታ ለማሻሻል ለመሳሰሉት ነገሮች 30 በመቶ፤ ለውስጥ አሰራር ማሻሻያ 45 በመቶ
እንዲሁም ለመማማር እና እድገት ከፋይናንስ በተሸለ 15 በመቶ የትኩረት አቅጣጫ
አስቀምጧል፡፡
በተዘጋጀው የግዢ አፈጻጸም መከታተያ ማንዋል መሰረት በማድረግ የክልል ግዢ ተቆጣጣሪ
አካላት በኦሮሚያ፤ አማራ፤ ትግራይ እና ደቡብ ህዝቦች ብሄር ብሄረሰቦች በክልላቸው
ተጨባጭ ሁኔታ የማጣጣም ስራ ማከናወናቸውን መከታተልን ከ 1 በመቶ በታች የሆነ
ትኩረት እንደሚሰጠውም አስፍሯል፡፡

ግምታዊ ዋጋቸው ከ 4 ሚሊየን ብር በላይ ሊያወጡ የሚችሉ የኮንትሮባንድ እቃዎች
የኢትዩጲያ ገቢዎች እና ጉምሩክ የጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ያዘ፡፡
በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ሊገቡና ሊወጡ ሲሉ የተያዙት እቃዎች ውስጥ ኤሌክትሮኒክስ፣
ምግብ ነክ ሸቀጦች፣ አዳዲስና ልባሽ ጨርቆች፣ ጫማዎች፣ ሲጋራ፣ መድሃኒት፣ የህንፃ
መሳሪያዎችና የቤት መገልገያ እቃዎች ሲሆኑ በወጭ ኮንትሮባንድ በኩል 73 የቀንድ ከብቶች፣
77 በጎች፣ 20 ፍየሎች፣ 5700 ኪ.ግ ጤፍ፣ 26 ኩንታል ቀይ ሽንኩርት፣ 3 ኩንታል ነጭ
ሽንኩርት፣ የተፈጨ ቡና እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት የመገበያያ ገንዘብ ይገኙበታል፡፡
እቃዎቹ የተያዙት ከሰኔ አንድ እስከ ሰኔ 30/2009 ዓ.ም. ሲሆን ጅግጅጋ ዙሪያ ቶጎ ጫሌ፣
ተፈሪ በር፣ ሐርሸን እና ለፈኢላ እቃዎቹ አካባቢ ነው የተያዙት፡፡

ሳውዲ አረብያ ህገ-ወጥ ስደተኞችን ከሀገሬ ይው ጡ ልኝ ያለችበት የጊዜ ገደብ ባቃበት እለት በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ የተባ ሁለት ኢትዩጲያውያን በሞት ተቀጥተዋል፡፡
በሪያድ ሁለት ኢትዩጲያውያን አንድ የፓኪስታን ዜግነት ያለው የታክሲ አሽከርካሪን በመዝረፍ እና በአስለት ወግተው በመግደል ከአንድ አመት በፊት ክስ ተመስርቶባቸው የነበረ ሲሆን ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የሞት ቅጣት ውሳኔው እንደተላለፈባቸው የሳውዲ አረቢያ የውስጥ ጉዳዩች ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በሀገሪቱ ያለውን የፍህ ስርአት ለማስጠበቅና የንጉሳዊ ስርአቱንም ደህንነት ለመጠበቅ እንዲሁም የሽሪያውን ህግ በጣሰ በማንኛውም ግለሰብ ላይ ለመፈጸም ሲባልም ይህ የፍርድ ውሳኔ መተግበሩን መግለጫው ጨምሮ ገልጾል፡፡
ሳውዲ አረቢያ የሰጠችው የ120 ቀናት የእፎይታ ጊዜ ሀምሌ 17 ቀን 2009 አ.ም መጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡
እጹብድንቅ ሀይሉ፡፡

የቃሊቲ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታ በመጨው ዓመት ታህሳስ ወር ይጠናቀቃል፡፡
በአዲስ አባባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን እየተገነባ ያለው የቃሊቲ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ጣቢያ የግንባታ ሂደት በቀጣይ ዓመት ታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ የግንባታ ሂደቱ ሲጠናቀቅ በስድስት ክፍለ ከተማ የሚገኙ 1.5 ሚሊዮን የአዲስ አባባ ከተማ ነዋሪዎችን ይጠቅማል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የስራ ሂደት መሪ የሆኑት አቶ አቶ እስጢፋኖስ ብስራት ያማጣሪያ ጣቢያው ከአለም ባንክ በተገኘ አንድ ሚሊየን ዶላርና የኢትዮጲ መንግስት ወጪ ባደረገው ስምንት መቶ ሚሊየን ብር ወጪ የሚገነባ ነው፡፡
7500 የማጣራት አቅም የነበረው የቃሊቲ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ የግንባታ የማስፋፊያ ሂደቱ ሲጠናቀቅ 100 ሺህ ሜትር ኩብ ያክል ፈሳሽ ማጣራት ይችላል ፡፡
የቃሊቲ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ጣቢያ አሁን ላይ የግንባታ ሂደቱ 90 ፐርሰንት የደረሰ ሲሆን የግንባታ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዋነኛነት ከሚሰጠው የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣራት ስራ የሚገኘው ውሃ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አቶ እስጢፋኖስ ለዛሚ ነግረዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ ባሏት ሶስት የፍሳሽ ማጣሪያዎች በምስራቅ ቦሌና የካን ክፍለ ከተሞችን በአቃቂ የአቃቂን አካባቢን አሁን ደግሞ የማስፋፊያ ስራው የሚካሄድለትና ስድስት ክፍለ ከተሞችን የሚይዘው የቃሊቲ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች ባለቤት ናት፡፡
ምትኬ ቶሌራ