አገር አቀፍ ዜናዎች

ነሐሴ 20/2008 ዓ.ም

የሃገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የ2008 ዓ.ም የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን የወሰዱ ተማሪዎች ውጤታቸውን ከሶስት ቀናት በኋላ አሳውቃለሁኝ ብሏል፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዘሪሁን ዱሬሳ እስከዛሬ በማህበራዊ ድረ-ገፆች የ10ኛ ክፍል ውጤት ይፋ ሆነ በሚል የተለቀቁት መረጃዎች ፍፁም ሀሰት ናቸው፤ ተፈታኞች ሊያምኑ አይገባም ያሉ ሲሆን ትክክለኛው የኤጀንሲው ውጤት በቀጣይ ቀናት የሚገለፅ እንደሆነም ሊያውቁ ይገባል ብለዋል፡፡

ውጤቱን ይፋ ለማድረግ የአጭር የጽሁፍ መልዕክት መቀበያ SMS እና የዌብ ሳይት ስራዎች ብቻ እንደቀሩም ዶ/ር ዘሪሁን ተናግረው እነዚህ ስራዎች እንደተጠናቀቁ ውጤቱ ይፋ ይሆናል ብለዋል፡፡

የ10ኛ ክፍል ፈተና ከግንቦት 17 እስከ ግንቦት 19 ቀን 2008 ዓ.ም መሰጠቱ የሚታወስ ሲሆን የ 12ኛ ክፍል ተፈታኞችን ጨምሮ ዘንድሮ ከ1.3 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ለፈተና ተቀምጠዋል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ነሐሴ 19/2008 ዓ.ም

ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመግባት 136 ሺህ 322 ተማሪዎች ፈተና የወሰዱ ሲሆን ወደ ከፍተኛ ትምህርት የመግቢያ ነጥባቸውም ተቆርጧል፡፡

በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቀን፤ በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማታ እንዲሁም በርቀት ትምህርት ትምህርታቸውን መከታተል የሚችሉት 295 እና ከዛ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ይሆናሉ የተባለ ሲሆን በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመደበኛ የትምህርት ዘርፍ ለመማር ተማሪዎች ባስመዘገቡት ውጤት ቅደም ተከተል መሰረት በውድድር ይሆናልም ተብሏል፡፡

በመሆኑም በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ፡-

  • የመደበኛ እና የማታ ተማሪዎች ለወንዶች 354 እና ከዛ በላይ፤ ለሴቶች 340 እና ከዛ በላይ ያመጡ
  • የግል ተፈታኝ ወንዶች 360 እና ከዛ በላይ፣ ሴቶች 355 እና ከዛ በላይ
  • በአዎንታዊ ድጋፍ መሰረትም ለታዳጊና የአርብቶ አደር ተማሪ ወንዶች 340 እና ከዛ በላይ፣ ሴቶች 335 እና ከዛ በላይ
  • መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች ወንዶችም ሴቶችም 297 እና ከዛ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች በመንግስት ከፍተኛ ተቋም ይመደባሉ፡፡

እንዲሁም በማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ፡-

  • መደበኛ እና የማታ ተማሪዎች ለወንዶች 330 እና ከዛ በላይ፤ ለሴቶች 320 እና ከዛ በላይ
  • የግል ተፈታኝ ወንዶች 360 እና ከዛ በላይ፤ ሴቶች 355 እና ከዛ በላይ
  • በአዎንታዊ ድጋፍ መሰረት ለታዳጊና የአርብቶ አደር ተማሪ ወንዶች 320 እና ከዛ በላይ ፤ ሴቶች 315 እና ከዛ በላይ
  • መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች ወንዶችም ሴቶችም 275 እና ከዛ በላይ
  • አይነስውራን ወንዶችም ሴቶችም 200 እና ከዛ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች በመንግስት ከፍተኛ ተቋም ይመደባሉ፡፡

ነሐሴ 12/2008 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹ ባለፈ የሃገር ውስጥ በረራ መዳረሻዎችን ለማስፋፋት እቅድ ይዞ እየሰራ ሲሆን የሽሬ፣ ጅንካ፣ ሐዋሳ እና ሮቤ ኤርፖርቶች የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳ እና መዳረሻ መንገድ ግንባታ ስራ በአብዛኛው ግንባታቸው መጠናቀቁን ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት ተናግረዋል፡፡

የባህር ዳር ግንቦት 20 ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳ ማስፋፊያ እና የላሊበላ ኤርፖርት የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳ እድሳት እየተከናወነ ነውም ብለዋል፡፡

በደብረ ማርቆስ፣ ቴፒ፣ በነገሌ ቦረና እና በሽላቦ አካባቢዎች ለቀላል አውሮፕላን ማረፊያ የሚሆን የቦታ መረጣ ለማከናወን ዓለም አቀፍ ደረጃውን መሰረት አድርጎ የቅድመ ዝግጅት ስራ መካሄዱንና በአራቱም አካባቢዎች የቦታ መረጣ ተከናውኖ ለየክልሉ አስተዳደር ገለፃ መደረጉን አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት ተናግረዋል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ነሐሴ 12/2008 ዓ.ም

በበጀት ዓመቱ በሁሉም የአገልግሎት ዓይነቶች የደንበኞች ብዛት 47.5 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ከዚህም ውስጥ የሞባይል ደንበኞች ብዛት 45.96 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን የኢንተርኔት እና ዳታ ተጠቃሚዎች ቁጥር በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ 13.6 ሚሊዮን መድረሱ ታውቋል፤ የመደበኛ ስልክ ደንበኞች ቁጥርም 1.1 ሚሊዮን ደርሷል፡፡

በ2008 ዓ.ም የተገኘው አጠቃላይ ገቢ 28 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህም የእቅዱን 73 ከመቶ አፈፃፀም ሲያሳይ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ30 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡

የሞባይል አገልግሎት ገቢ ከአጠቃላይ ገቢ 69 ከመቶ ሲሸፍን፤ ዳታ እና ኢንተርኔት 21 ከመቶ እንዲሁም ዓለም አቀፍ አገልግሎት እና ሮሚንግ 6 ከመቶ ድርሻ ይዘዋል፡፡

ኩባንያው በበጀት ዓመቱ 23 አዳዲስ አገልግሎቶችን ወደ ተጠቃሚዎች ማቅረብ ችሏል፡፡

ነሐሴ 09/2008 ዓ.ም

የ12ኛ ክፍል አገርአቀፍ ፈተና ውጤት ይፋ መሆኑን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገብረእግዚአብሄር አስታውቀዋል፡፡

ተማሪዎች ውጤታቸውን በኤጀንሲው ዌብሳትይት www.neaea.gov.et ላይ Student result የሚለው ቦታ ላይ የመለያ ቁጥራቸውን በማስገባት ለማየት ይቻላሉ፡፡

ውጤት ለማየት ሌላኛው አማራጭ ደግሞ በነፃ አጭር የፅሁፍ መልክት 8181 ላይ RTW ብለው በመፃፍ ስፔስ በማድረግ የመለያ ቁጥራቸውን አስገብተው በመላክ ማወቅ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
ማለፊያ ነጥቡ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ዋና ዳይሪክተሩ ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መግቢያ ፈተና በመሰረቁ ምክንያት በተሰጠው ልዩ ትኩረት ቀን ከለሊት በመሰራቱ እንደሆነ የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ዳይሪክተር አቶ ረዲ ሺፋ አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም ኤጀንሲው ተጨማሪ 10 የማረሚያ ማሽኖች ገዝቶ ወደ ስራ በማስገባቱ ውጤቱን በአፋጣኝ ለማውጣት መቻሉን ገልፀዋል፡፡

የ10ኛ ክፍል ውጤትም ከነሐሴ 15 እስከ 30 ባለው ጊዜ ውስጥ ይፋ እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የ10ኛ ክፍል ውጤት ከ12ኞቹ የዘገየው የተፈታኞቹ ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ በመሆኑ ለማረም የበለጠ ጊዜ በመፍጀቱ እንደሆነ ነው አቶ ረዲ ያስታወቁት፡፡

- ምንጭ- የሃገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጄንሲ

ሐምሌ 17/2008 ዓ.ም

የአጣዳፊ ተቅማጥና ትዉከት ተላላፊ በሽታ ስርጭትን ለማቆም አሁንም የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከአ/አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን ሕብረተሰቡን በንቃት እንዲሳተፍ በማድረግ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዉ ተጠናክሮ ቀጥሏል ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኮልፌ ቀራንዮ፣ በንፋስ ስልክና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች የታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን በሌሎች ክፍለ ከተማዎች ቁጥሩ ሳይቀንስ ባለበት እየሄደ በመሆኑ የታማሚዎች ቁጥር የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ ነዉ፡፡

በተዋቀሩ 29 የህክምና ጣቢያዎች ላለፉት ሳምንታት ታማሚዎች የህክምና አገልግሎት እያገኙ ወደየቤታቸዉ እየተመለሱ ሲሆን ከ200 በላይ ታማሚዎች በህክምና ላይ መሆናቸውም ታውቋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ግን ሞት አለመኖሩ ታውቋል ፡፡
የበሽታዉን መነሻዎች ለማወቅና ለመቆጣጠር ባለሙያዎች ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ያሉ እንደመሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ወንዞችና ምንጮች በበሽታ አምጪ ተህዋሲያን የተበከሉ መሆናቸው ታወቋል፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ የባለሙያዎች ዳሰሳና ምርመራ የተበከሉ የስጋና የአትክልት ውጤቶችን በጥሬያቸዉ የተመገቡ ሰዎች ለበሽታዉ መጋለጣቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ በመጠቃት ላይ ያሉ ነዋሪዎች በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ወንዞች፣ ምንጮች እና ንፅህና በጎደለው ውሃ ታጥበዉ የቀረቡ በህገወጥ የታረዱ የስጋ ዉጤቶችን በዱለት፣ በሰንበርና ምላስ፣ በክትፎና በጥሬ ስጋነት እንዲሁም አትክልቶችን ሳያበስሉ የተመገቡ ሰዎች እንደሆኑ የህክምና መረጃዎች አሳይተዋል፡፡
በሌላ በኩል በተበከሉ የወንዝ ፣የምንጭ፣ የቦይ፣ ወራጅ ዉሃ ዉሃዎችን በመጠቀም ምግብ የሚያዘጋጁ፣ የምግብ እቃዎችን፣ ልዩ ልዩ የቤት መገልገያ ቁሳቁሶችን መኪናን ጨምሮ የሚያጥቡ የሚያሳጥቡና የተበከሉ ፍሳሾችን ረግጠዉ ሳያጸዱ ወደ መኖሪያ ቤታቸዉ የሚገቡ ሰዎችና ቤተሰቦች ለበሽታው እንደሚጋለጡ የታወቀ ሲሆን በማንኛውም ሰዓት ጥንቃቄ እንዳይጎድልም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

(ምንጭ፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር)

ሐምሌ 14/2008 ዓ.ም

ባለፉት ጊዜያት በገጠመው ህመም ምክንያት ከሀገር ውጭ እና እዚሁ በአዲስ ሕይወት ሆስፒታል ተኝቶ ህክምና ሲከታተል የቆየው አርቲስት አባተ መኩሪያ ከህመሙ ማገገም ባለመቻሉ ትናንት ማምሻውን አርፏል፡፡

ዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም በአንጋፋው የትያትር ባለሙያ ሞት የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቹ እና ለወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን ይመኛል!

ሐምሌ 01/2008 ዓ.ም

በ1987 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ከተቋቋመበት አመት ጀምሮ 125 ሺ ለሚሆኑ ሴቶችና ከዚህ ቁጥር በእጥፉ ለሚልቁ ህጻናት ነጻ የህግ ከለላ ሰጥቷል፡፡

በሃገራችን በጠበቆች የስነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 57/1999 ነጻ የህግ አገልግሎት ጉዳይ በአንቀጽ 49 በግልጽ ሰፍሯል፡፡ ህጉ የጥብቅና ፈቃድ ያለው ባለሙያ በአመት 50 ሰአት ያህል ነጻ አገልግሎት ይስጥ ቢልም የኢትዮጲያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር አባላት ግን በአመት 400 ሰአታት ያህል ነጻ የህግ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ስብስብ ሆኗል፡፡

ማኅበሩ በአጠቃላይ 60 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን 59 በክልል ከተሞች እና 1 በአዲስ አበባ በመክፈት በአመት ለ10 ሺ አቅመ ደካማ ሴቶች የማማከር የማሰልጠንና የጥብቅና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ማህበሩ በተለይ የፍርድ ቤት ክርክር ያለባቸውና በገንዘብ እጥረት ምክንያት የክስ ሂደታቸውን የሚያቋርጡ ሴቶችን በገንዘብ ለመደገፍ ቋሚ የገንዘብ ምንጭ የሌለው በመሆኑ መርዳት የሚችለውን ያህል መደገፍ እንዳልቻለ የማህበሩ ዳይሬክተር ወይዘሮ ዜናዬ ታደሰ ይናገራሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሴቶች ራሳቸውን ወክለው የፍርድ ቤት ክርክርን መምራት እንዲችሉ የሚያግዙ ስልጠናዎችን ይሰጥ የነበረው ማህበሩ ያለምንም ጠበቃ ሴቶቹ ራሳቸን ችለው ለመከራከር የሚያስችላቸውን አቅም ሲፈጥር የቆየ ቢሆንም አሁን ግን በገንዘብ እጥረት ምክንያት ይሄንም መከወን እንዳልቻለ ዳይሬክተሯ ይናገራሉ፡፡

ማህበሩ የገንዘብ አቅም ለመፍጠርና ለሴቶችና ህጻናት የሚሰጠውን የነጻ የህግ አገልገሎት በሰፊው ተደራሽ ለማድረግ እንዲችል የገቢ ማሰባሰቢያ ምሽት አዘጋጅተዋል፡፡ የገቢ ማሰባሰቢያ ምሽቱ ሐምሌ 7 ቀን 2008 አ.ም የሚካሄድ ሲሆን ቦታውም ደሳለኝ ሆቴል ነው ተብሏል፡፡ የመግቢያ ዋጋውም 1000 ብር ሲሆን 10 ሺ ብር ዋጋ ያላቸው ጠረንጴዛዎችንም እስፖንሰር ለሚያደርጉ አካላት አዘጋጅተዋል፡፡ ገቢውም በገንዘብ እጥረት ምክንያት የክርክር ሂደታቸውን የሚያቋርጡ ሴቶችን ለመደገፍና ራስን ወክሎ በፍርድ ቤት ክርክር የመምራት ክህሎት ስልጠናዎችን ለመስጠት የሚውል ይሆናል፡፡ ማህበሩን በነጻ የሚያገለግሉ 20 የህግ ባለሙያዎች ያሉት ሲሆን ዘጠኙ ወንዶች ናቸው ተብሏል፡፡

ሰባ ከመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለቤት ውስጥ ጥቃት ተጋላጭ ናቸው የሚሉት የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር አባላት ይሄ ጉዳይ የሚያሳስበው ወገን በሙሉ ሐምሌ 7/2008 ዓ.ም በደሳለኝ ሆቴል በመገኘት ድጋፉን ያሳየን ይላሉ፡፡ (እንየው ቢሆነኝ)

ሰኔ 24/2008 ዓ.ም

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የሚገኘው የእንስሳት ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሀገሪቱ የመጀመሪያውን የእንስሳት ሆስፒታል ገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡ ሆስፒታሉ ላብራቶሪዎችን ጨምሮ በቁሳቁስና በባለሙያ የተደራጀ ሲሆን ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችም ተገጥመውለታል፡፡

በማዕከሉ ከቀላል ጀምሮ እስከ ቀዶ ጥገና የሚደርስ ህክምና እንዲሁም ከድንገተኛ ጀምሮ እስከ 4 ቀን ድረስ ተኝተው ለሚታከሙ እንስሳት የህክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ ለሰው ልጆች በህክምና ተቋማት እንደሚያገኙት አገልግሎት ካርድ ማውጣት የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህም ባመጧቸው ሰዎች አማካኝነት ከስማቸው ጀምሮ ሌሎች መረጃዎች ይመዘገባሉ፡፡

በመቀሌ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮችም በከብቶቻቸውም ሆነ በቤት እንስሳቶቻቸው የሚደርሱ የጤና ቸግሮችን ተከትሎ ወደ ሆስፒታሉ በማምጣት ህክምና እንዲያገኙ ያደርጋሉ፡፡

በየቀኑ 5 የሚደርሱ ስፖሻሊስት ሀኪሞች ለእንስሳቱ ክትትል እንደሚያደርጉ እና ከመድሃኒት ጀምሮ አስፈላጊ ቁሳቁሶች በሆስፒታሉ በመገኘታቸውም ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ መቻሉን ዶ/ር በሪሁን የጤና ሳይንስ ኮሌጁ ዲን ተናግረዋል፡፡

በሆስፒታሉ የተለያዩ የምርምር ስራዎች የሚከናወኑ ሲሆን ይህም አዳዲስ ግኝቶችና ሰፋፊ ተግባራትን ለማከናወን አስችሏልም ተብሏል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

ሰኔ 22/2008 ዓ.ም

አደጋው የደረሰው በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 12፡30 ሰዓት ከውቅሮ ወደ መቐለ በሚመለሱበት ወቅት ሲሆን በሰዓቱ ከፍተኛ ዝናብ ጥሎ የነበርና ላንድክሩዘሩ ተሸከርካሪ በመገልበጡ ወ/ሮ ሙሉ ካህሳይ የትግራይ ክልል ሴቶች ቢሮ ሃላፊን ጨምሮ 4 ባለሙያዎች ህይወታቸውን ሊያጡ ችለዋል፡፡

የቀብር ስነ-ስርዓታቸውም በዛሬው ዕለት እየተፈፀመ ነው፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

ሰኔ 21/2008 ዓ.ም

የአዲሰ አበባ ትምህርት ቢሮ በከተማው የሚገኙና በትምህርት ጥራት መስፈርት ከተገቢው ነጥብ በታች ያመጡ ከ100 በላይ ትምህርት ቤቶች በማስተማር ስራ ላይ እንደማይቀጥሉ አሳውቋል፡፡ የትምህርት ቤቶቹ ማንነት ይፋ ባይደረግም ትምህርት ቤቶቹ በጥራት ደረጃው ተገቢውን መስፈርት ማሟላት ያቃታቸው ናቸው ተብሏል፡፡ የአቋራጭ ተማሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ ሰርቻለሁ የሚለው ትምህርት ቢሮው 10,173 ያህል ህጻናት እድሜያቸው ለትምህት ቢደርስም ወደ ትምህርት ቤት ግን እንዳልተወሰዱ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ በአዲስ አበባ በሁሉም የመንግስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው እንዲሆኑ የክረምት የትምህርት እድል መሰጠቱን አቶ አበበ ቸርነት የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ለዛሚ ተናግረዋል፡፡ (እንየው ቢሆነኝ)

ሰኔ 17/2008 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ከ24 የማያንሱ ፓርኮች፣ የእንስሳት መጠለያዎችና የቱሪስት መዳረሻዎች የሚገኙ ሲሆን እነዚህም የተፈጥሮ ሀብቶች የሀገሪቱን የገቢ ምንጭ በአንድ ጎን እየደገፉ በሌላ ጎናቸዉ የተፈጥሮ ሀብቷን እያስተዋወቁ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጽያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት እና መረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዘሪሁን ዘዉዴ ለዛሚ እንደተናገሩት ካለፉት አመታት በተሻለ መልኩ የተፈጥሮ ሀብቶቻችን የገቢ ምንጭነታቸው ጨምሯል ያሉ ሲሆን ዘርፉም ከወትሮው በተለየ መልኩ ትኩረት ተሠጥቶት እየተሰራበት ነዉ ብለዋል። ባለፉት አመታት ከጎብኚዎች ከ50 ሚሊየን ብር ያልበለጠ ገቢ ነበር ይገኝ የነበረዉ ያሉን አቶ ዘሪሁን ዘንድሮ ይህ ገቢ ወደ 80 ሚሊየን ብር ከፍ ማለቱን ነግረዉናል። የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ፣ የስንቅሌ ቆርኪዎች ፓርክ እና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ገቢዉ ከተገኘባቸዉ ፓርኮች መካከል ተጠቃሾቹ ናቸውም ተብሏል። (እንየው ቢሆነኝ)

ሰኔ 16/2008 ዓ.ም

ከዋናው ቢሮ በተጨማሪ በስድስት የክልል ከተሞች ቅርንጫፎችን በመክፈት የቁጥጥር ስራ ላይ የተሰማራው ባለስልጣኑ በድህረ ምልከታ ወቅት ቀድሞ ከተፈቀደላቸው የምግብ ምርትና ዝግጅት ውጭ ፍቃድ ባልወሰዱበት ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ድርጅቶች ጉዳይ እንዳሳሰበው ተናግሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት 30 የወተት አምራች ኩባንያዎች ከባለስልጣኑ ፈቃድ ወስደው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ከንግድ ቢሮ ጋር በመተባበር እየሰራሁ ነው የሚለው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እስከ ስድስት ወር ድረስ የምርት ማምረት እገዳ በመጣል የማስተካከያ እርምጃ የተወሰደባቸው ድርጅቶችም መኖራቸውን አሳውቋል፡፡ በቅርቡ በለስላሳ መጠጦች ምክንያት የሰዎች ህይወት አልፏል መባሉን ተከትሎ የምርመራና ቁጥጥር ስራ የሰራው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን ማረጋገጥ እንደቻለ የኢትዮጲያ የምግብ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብ ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ግርማ ለዛሚ ተናግረዋል፡፡ (እንየው ቢሆነኝ)

ሰኔ 11/2008 ዓ.ም

የደቡብ ኮሪያ መንግስት በትናንትናው ዕለት 500,000 የአሜሪካን ዶላር የሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረጉ ተገልጧል፡፡ ይኸው ድጋፍ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ሲሆን የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ቲም ሙን ሀን እንዲሁም ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉነህ ወልደማሪያም በተገኙበት  በብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጽ/ቤት ርክክቡ ተደርጓል፡፡

በአገራችን 2007/2008 ዓ.ም በኤልኒኖ ክስተት የመኸርና የበልግ ዝናብ እጥረት በማጋጠሙ በተከሰተው ድርቅ 10.2 ሚሊዮን ህዝብ ለጉዳት መጋለጡን መሰረት በማድረግ በጃንዋሪ 2016 የወጣውን የሰብዓዊ ሰነድ መነሻ በማድረግ በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እንዲውል የተሰጠ የመጀመሪያ ድጋፍ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ኢትዮጵያና ደቡብ ኮርያ ካላቸው የቆየ ወዳጅነትና ትብብርም በተጨማሪ በቀጣይ አገሪቱ በምታደርጋቸው የልማት እንቅስቃሴዎችም የደቡብ ኮርያ መንግስት የቅርብ ድጋፍ እንደማይለይ አምባሳደር ቲም ሙን ሀን ገልፀዋል፡፡

ይኸው ድጋፍ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ድርቁ በተከሰተባቸው የተለያዩ አካባቢዎች እየተደረገ ባለው ድጋፍ ተጨማሪ በመሆን ጥቅም ላይ እንደሚውል አቶ ሙሉነህ ወ/ማሪያም ገልፀዋል፡፡

ምንጭ- ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን

ሰኔ 09/2008 ዓ.ም

የብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሀብተማሪያም ደመወዝ እንደገለጹት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከመደበኛ እና ከበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች ከ128 ሺህ ዩኒት በላይ ደም መሰብሰቡን ገልፀዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የዓለም ደም ለጋሾች ቀን ዘመቻ በዋናነት የበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች በለገሱት ደም ህይወታቸው የተረፉ ሰዎችን ታሪክ ማንፀባረቅና የመደበኛ በጎ ፍቃድ ደም ለጋሾች ህይወት አድን ስራን ቀጣይ እንዲያደርጉት ማነቃቃት፣ እንዲሁም ህብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ ጤንነቱ ተጠብቆ በበጎ ፍቃድ ደም እንዲለግስ ማነቃቃት ነው ብለዋል፡፡

አስተማማኝ የደም አቅርቦት የህመምተኞችን ህይወት በማራዘም የተሻለ ህይወት እንዲመሩ ከማስቻሉም በላይ ውስብስብ የሆኑ የህክምና ስራዎችን፣ የእናቶችና የህፃናት ህይወት የማዳን ተግባርን በከፍተኛ ደረጃ ማቃለል ችሏል፡፡ በአለም ላይም በብዙ አገሮች በቂና ደህንነቱ የተጠበቀ ደም የማቅረብ ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው የሚታወቅ ሲሆን በዋናነት በቂና አስተማማኝ የደም አቅርቦት ሊገኝ የሚችለው ያለማቋረጥ ከመደበኛ የበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች በሚገኝ የደም ልገሳ ነው፡፡ ከትናንት በስቲያ መከበር የጀመረው የበዓል ስነ-ሥርዓቱም እስከ አመቱ መጨረሻ ድረስ የሚቀጥል ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ለ20 ሚሊዮን ህዝብ የፅሑፍ መልእክት የሚላክ፣ ከሚመለከታቸው አመራሮች ጋር የእግር ጉዞ የሚደረግ፣ ደም ለጋሾችን የማመስገንና እውቅና የመስጠት፣ ስለ ደም ባንክ አገልግሎት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን የመስራትና ከአዲስ አበባ ወጣት ፎረሞች ጋር በመሆን ደም የማስለገስ ተግባራት እንደሚከናወኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የዘንድሮ የደም ለጋሾች ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ13ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ12ኛ ጊዜ መከበር የጀመረ ሲሆን በአሉም “ደም ያስተሳስረናል” በሚል መሪ ቃል እስከ አመቱ መጨረሻ ድረስ ይቀጥላል፡፡

ምንጭ - የኢፌዴሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

ግንቦት 29/2008 ዓ.ም

ከቀኑ 9፡30 ሰዓት በአዲስ አበባ የጣለው በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢን፣ ሜትሮሎጂ እና ተክለሀይማኖት አካባቢዎችን በጎርፍ ያጥለቀለቀ ሲሆን በሰው ላይ ምንም ጉዳት አላደረሰም ተብሏል፡፡ ጎርፏ ስድስት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የገባ ሲሆን ሶስት መቶ አስር ሺ ብር የሚገመት የንብረት ውድመትንም አስከትሏል፡፡

የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ሰራተኞች በየመኖሪያ ቤቶቹ የገባውን ውሀ ለማውጣት ስድስት ሰዓታትን የፈጀ እርዳታንም ሲሰጡ እንደነበር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ንጋቱ ማሞ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ግንቦት 29/2008 ዓ.ም

እሁድ ምሽት 2፡30 ሰዓት በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የተማሪዎች የመኝታ ፍራሽ ማከማቻ በሆነ ክፍል ውስጥ የተነሳው እሳት አራት ተማሪዎች በጭስ እንዲታፈኑ ያደረገ ሲሆን አንድ መቶ ሺ ብር የሚገመት የንብረት ውድመትም አስከትሏል ሲሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ንጋቱ ማሞ ለዛሚ ተናግረዋል፡፡

አደጋ የደረሰባቸው ሁለት ተማሪዎች በሚኒሊክ ሆስፒታል ሁለቱ ደግሞ በየካ ጤና ጣቢያ የህክምና እርዳታን እያገኙ እንደሆነ የተናገሩት ሀላፊው የእሳቱ ትክክለኛ መንስኤም በፖሊስ እየተጣራ እንደሆነ አክለው ተናግረዋል፡፡

እሳቱን ለማጥፋት 12 ሺ ሊትር ውሀ፣ 14 ባለሙያዎች እና 2 አምቡላንስ እንዲሁም ሁለት የአደጋ መከላከያ መኪናዎች ተሰማርተው እንደነበርም ተገልጧል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ግንቦት 23/2008 ዓ.ም

የኮድ ቁጥሩ 12 የሆነውና ለ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ወሳጆች ቀርቦ የነበረው የእንግሊዘኛ ፈተና ተሰርቆ መውጣቱ በመታወቁ ፈተናው እንዲሰረዝ መደረጉና ሌሎች ፈተናዎችም ላለመሰረቃቸው ማረጋገጫ ባለመኖሩ አጠቃላይ የፈተና ሂደቱ እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ዛሚ ከትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ምስጋና ፀጋዬ እንደሰማው እንዲህ አይነት ችግር ሲያጋጥም እንደ አማራጭ የሚቀርቡና ለመጠባበቂያ ተብለው ተዘጋጅተው የነበሩ ፈተናዎች በመኖራቸው ፈተናው ከአንድ ወር በኋላ ማለትም ከሰኔ 27 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ድረስ በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች ዳግም ይሰጣል ብለዋል፡፡ አቶ ምስጋና ፀጋዬ አክለውም የፈተና ዝግጅቱና አሰጣጡ በከፍተኛ ጥንቃቄና ጥበቃ የሚከናወን ይሆናል ያሉ ሲሆን የህትመትና የስርጭት ስራውም በተመሳሳይ ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግበታል ብለዋል፤ ተፈታኞችም ተገቢውን ዝግጅት አድርገው ከአንድ ወር በኋላ ዳግም ለፈተና ለመቀመጥ ይዘጋጁ ሲሉ ለዛሚ 90.7 ኤፍ.ኤም ተናግረዋል፡፡ (ያልፋል አሻግር)